በኦሮሚያ እና ሲዳማ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ አምስት ሰዎች ተገደሉ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን እና በሲዳማ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ከትላንት በስቲያ እሁድ መጋቢት 25 ምሽት በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን የሲዳማ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በግጭቱ በጥይት ከቆሰሉ አስራ አምስት ሰዎች ውስጥ ሶስቱ የደረሰባቸው ጉዳት “ከባድ” የሚባል እንደሆነ የህክምና ባለሙያዎች አስታውቀዋል።

የእሁዱ ግጭት የተቀሰቀሰው፤ በሲዳማ ክልል፣ ጪሪ ወረዳ፣ ሀሌላ ቀበሌ ነዋሪዎች ዘንድ ታዋቂ የሆኑ የሀገር ሽማግሌ መገደላቸውን ተከትሎ እንደሆነ አቶ አለማየሁ ገልጸዋል። አዴ ሎኬ ዮኔ የተባሉት እኚሁ አባት ከትላንት በስቲያ ምሽት አራት ሰዓት ገደማ የተገደሉት “ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ነው” ብለዋል።

ይህ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በሀሌላ ቀበሌ የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ አጎራባች ቀበሌዎች መስፋፋቱን አቶ አለማየሁ አስረድተዋል። ግጭቱ በሲዳማ ክልል፣ ጪሪ ወረዳ ስር የምትገኘውን ሱጫ ቀበሌን እንደዚሁም በኦሮሚያ ክልል ሻምበል እና ውሮ ቀበሌዎችን ማዳረሱን አመልክተዋል። በአካባቢዎቹ የተፈጠረውን ክስተት “ሁከት” ሲሉ የጠሩት የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ  ቢሮ ኃላፊው፤ “የብሔር መልክ እንዲይዝ የተደረገ ሙከራ” እንደነበርም ጠቁመዋል።

በግጭቱ እስካሁን ከሲዳማ ክልል በኩል የሀገር ሽማግሌውን ጨምሮ ቢያንስ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ፤ በኦሮሚያ በኩል ደግሞ የሶስት ሰዎች ህይወት እንዳለፈ አቶ አለማየሁ ገልጸዋል። በሲዳማ ክልል፣ ቦና ዙሪያ ወረዳ ስር ያለው የቦና አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ መንገሻ ቦኮ በግጭቱ በጥይት የቆሰሉ ሰባት ሰዎች ወደ ሆስፒታላቸው መምጣታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ቆስለው ለህክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታሉ ከመጡት ሰዎች ውስጥ የተወሰኑት ግጭቱ የተቀሰቀሰበት የጪሬ ወረዳ ነዋሪ መሆናቸውን የሚናገሩት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ፤ ሌሎቹ ተጎጂዎች በበንሳ ወረዳ ስር ባሉት ቀጠና፣ ከራሞ እና ሀማሾ ቀበሌዎች እንዲሁም የዳኤላ ወረዳ፣ ኤቻማ ቀበሌ ነዋሪዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። ከእነዚህ ተጎጂዎች መካከል ሶስቱ በከባድ ሁኔታ በመጎዳታቸው ወደ ሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል መላካቸውን አቶ መንገሻ አክለዋል።

በበንሳ ወረዳ ስር ያለው የዳዬ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ቱኬ በበኩላቸው፤ ዘጠኝ ቁስለኞች ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን ገልጸው፤ ከእነርሱ ውስጥ አንደኛው ታካሚ በህክምና እርዳታ ላይ እያለ ሕይወቱ ማለፉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሁሉም ተጎጂዎች በጥይት የቆሰሉ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በትላንት በስቲያው ግጭት ህይወታቸውን ካጡ እና ከቆሰሉ ሰዎች በተጨማሪ፤ በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን የሲዳማ ክልል የሲዳማ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል። የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ግጭቱን ለማርገብ እርምጃዎች መውሰዳቸውን የጠቀሱት አቶ አለማየሁ፤ ከዚህ በተጨማሪ የሁለቱ ክልል የመንግስት ኃላፊዎች በአባ ገዳዎች እና በሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች የታገዘ ምክክር በማድረግ ግጭቱ እንዲቆም ማድረጋቸውን አብራርተዋል።

“የጸጥታ አካል በተደራጀ መንገድ ገብቶ እያረጋጋ ነው ያለው። ወደ ሌላ አዝማሚያ የሚያስብ አካል ካለ ደግሞ እርምጃም እንዲወስዱ [ታዝዘዋል]። የጸጥታ ኃይሉ፤ በዚህ አጋጣሚ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ካለ እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ይህንን ስራ እየሰራ ነው የሚገኘው” ሲሉ አቶ አለማየሁ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል።

የጥቃቱን ፈጻሚዎች ማንነት በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የሲዳማ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ፤ ታጣቂዎቹን ለመለየት ማጣራት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል። ሆኖም “በኦሮሚያ ክልል ታጥቀው የሚዞሩ ታጣቂዎች ሊሆኑ ይችላሉ” የሚል ግምት መኖሩንም ጠቁመዋል። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊን እና የምዕራብ አርሲ ዞን አስተዳዳሪን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)