ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በ81 ሚሊዮን ብር ወጭ ሁለት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ሊያደርግ ነው።

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በ81 ሚሊዮን ብር ወጭ ሁለት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ሊያደርግ ነው።

ሁለቱ ፕሮጀክቶች የሚተገበሩት በማዕከላዊና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ተፈፃሚ የሚሆኑ ሲሆን አንደኛው በ43 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ የሚተገበረው “ኢዱኬሽን ካንኖት ዌይት ፕሮጀክት” ሲሆን ሁለተኛው “ቤቴ ፕሮጀክት” ከ38 ሚሊየን ብር በላይ የተያዘለት ፕሮጀክት ነው።

“ኢዱኬሽን ካንኖት ዌይት ፕሮጀክት” የተሰኘው ፕሮጀክት በጭልጋ ቁጥር 1 እና ጭልጋ ቁጥር 2 እንዲሁም ምሥራቅና ምዕራብ ደምቢያ ወረዳዎች ይተገበራል ሲሉ የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የአማራ ክልል ዳይሬክተር አቶ አሰፋ እሸቴ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ከአሁን በፊት በተጠቀሱት አካባቢወች የአደጋ ጊዜ ተጋላጭ ህጻናት ለአንድ ዓመት ያክል ሲሠራ የቆየ ሲሆን አሁን ወደ ሁለተኛ ምዕራፉ ገብቷል። ባለፈው አንድ ዓመት ሰባት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶቾች ላይ ሠርቷል፡፡

በዚህ ዓመት ወደ 11 ትምህርት ቤቶች አገልግሎቱን በማስፋት 9 ሺህ 152 ህፃናት ምቹ ከለላና ክህሎት እንዲያገኙ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል።

ሁለተኛው “ቤቴ ፕሮጀክት” በደባርቅና ዳባት ወረዳዎች በአዲስ የሚተገበር የዘጠኝ ወር ፕሮጀክት ሲሆን 22 ሺህ 259 የግጭት ተጋላጭ ህጻናት ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሮጀክቶቹ የታለመላቸውን የልማት ውጥን እውን ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በጎንደር ከተማ ምክክር ተደርጓል።

ሁለቱ ፕሮጀክቶች በዋናነት በህጻናት ጥበቃና ትምህርት ዙሪያ ላይ የሚያተኩሩ ሲሆኑ 31 ሺህ 411 የግጭት ተጋላጭ ህጻናትን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሏል። (አሚኮ)