“ስጋት ከተጋረጠብኝ ኒውክሌር ልጠቀም እችላለሁ” ሩሲያ

“ስጋት ከተጋረጠብኝ ኒውክሌር ልጠቀም እችላለሁ” ሩሲያ
ዩናይትድ ስቴትስ ኒውክሌርን በተመለከተ ሩሲያ የምታራምደውን አቋም አወገዘች፡፡ ፔንታጎን ሩሲያ ኒውክሌርን ጥቅም ላይ ለማዋል ፍላጎት ማሳየቷን አጣጥሏል ፡፡
አደገኛ ጉዳይ ነው ብሎታል ፡፡ የክሪሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ ነው ከነጩ ቤተ መንግስት በኩል ስጋት አለን የሚል አስተያየት እየተሰነዘረ ያለው ፡፡
ቃል አቀባዩ እንደሚሉት ሩሲያ ስጋት የተጋረጠባት መስሎ ከታየት እንዲህ አይነቱን የጦር ማሳሪያ ልትጠቀመው ትችላለች ፡፡ ሩሲያ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኒውክሌር አረር ያላት አገር ከመሆኗም ባሻገር ብሄራዊ ስጋት ከተጋረጠብኝ አደርገዋለሁ ማለቷ የዋሽንግተንን ፖለቲከኞች አስደንግጧል፡፡
የዩናይትድ ስቴትሱ የመከላከያ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ሁኔታው አደገኛ መሆኑን አልሸሸጉም ፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው ኒውክሌር የተጠቀ ኃይል በዚህ መንገድ መታየት እና እንቅስቃሴ ማድረግ ባልኖረበትም ይላሉ፡፡ ፔንታጎን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው ነው ተብሏል ፡፡ ሞስኮ ኒውክሌር ለመጠቀም የሚያደርስ ስጋት አይጋረጥባትም ፤ ወደ ኒውክሌር ጦርነት ትገባለች ተብሎም አይታሰብም የሚሉ ተንታኞች ይኑሩ እንጂ ፑቲን ቀደም ሲል የኒውክሌር ኃይሉን ነቅተህ ጠብቅ ማለታቸው የሚዘነጋ አይደለም ፡፡