ማንነታቸው ያልታወቁና በቡድን በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በጉራፈርዳ ግድያና ዝርፊያ እየፈፀሙ ነው ተባለ

የጉራፈረዳ ነዋሪዎች በግድያ እና ዝርፍያ እየተሰቃዩ ነው

በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ግድያ እና ዝርፍያ ህዝቡን ምሬት ውስጥ መክተቱን ሰምተናል

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንነታቸው ያልታወቁና በቡድን በሚንቀሳቀሱ ታጠቂዎች ተደጋጋሚ ትንኮሳ ፣የከብትና የጦር መሳሪያ ዝርፊያ እየተፈጸመ እንደሚገኝ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በቤንች ሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ ካሉ ስድስት ቀበሌዎች ውስጥ አንዱ በሆነው ኩጃ ቀበሌ ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋጋሚ የከብት ዝርፊያ እንዲሁም በነዋሪዎች ላይ ግድያ እየተፈጸመ መሆኑን የቀበሌው ነዋሪ የሆነው ግለሰብ ለጣቢያችን ተናግሯል፡፡

ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መመርያ ሀላፊ አቶ ተስፋይ ጊስካር እንደነገሩን ለጸጥታው መደፍረስ በዋናነት በቀበሌዋ ከፍተኛ የሆነ ህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውርና ሽያጭ መበራከት ዋናው ምክንያት ነው ያሉ ሲሆን እንዲህ ያለውን ድርጊት ህብረተሰቡ በአንድነት አለመታገሉ ደግሞ ሌላው ምክንያት ነው ብለውናል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንነታቸው ያልታወቁና ታጥቀው በቡድን በሚንቀሳቀሱ አካላት ተደጋጋሚ የከብትና የጦር መሳሪያ ዝርፊያ እየተካሄደ ሲሆን ንጹሀን ላይ ደግሞ ግድያ እየተፈፀመ ነው ሲሊ አቶ ተስፋይ አረጋግጠውልናል፡፡

ቀበሌዋ ለጋምቤላ ክልል አኙዋክ ዞን ዲማ ወረዳና ምዕራብ ኦሞ ዞን አዋሳኝ በመሆኗ ከዚህ ቀደም ከሱርማ ወረዳ አካባቢ ተነስተው በሚመጡ ሽፍቶች የከብት ዝርፊያ ይፈጸም እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አሁንም ያለው ከዚሁ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የተናገሩት ሀላፊው ዝርፍያው እና ግድያው የሚፈጸመው ጨለማን ተገን አድርገው በሚንቀሳቀሱና በጫካ የሚደበቁ ሰርጎ ገብ ታጣቂዎች እንደሆነ ነግረውናል፡፡

በትላንትናው እለትም በጉራ ፈርዳ አንድ ግለሰብ በሽፍቶች እንደተገደለ እና ከብቶቹም እንደተዘረፉበት ነው አቶ ተስፋዬ የተናገሩት፡፡

አሁን በኩጃ ቀበሌ ለሚታየው የጸጥታ መደፍረስ ህብረተሰቡና የወረዳው ጸጥታና ፖሊስ መዋቅር ወንጀልን በጋራ ለመከላከል የሚያደርገው ቅንጅት አናሳነት ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ በጉያው የተመሸጉ ህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ነጋዴዎች ፣ ደላላዎችና አስተላላፊዎችን ለህግ አካላት አሳልፎ እስካልሰጠና ተደራጅቶ ወንጀልን እስካልተከላከለ ድረስ መሰል የጸጥታ ችግሮች በፖሊስና በጸጥታ መዋቅሩ ስራ ብቻ የሚፈቱ አይሆኑም ብለዋል፡፡

በቀጠናው ከፍተኛ የጦር መሳሪያና የጥይት ፍሬ ዝውውርና ሽያጭ የሚፈጸምበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ኃላፊው ገልጸው የወረዳው የጸጥታ መዋቅሮች ችግሩን ለመፍታት ከህዝቡ ጋር እየመከርንበት እንገኛለን ሲሉ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም