ሱማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ 1.1 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸው ተገለጸ

በክልሉ እስካሁን የዘነበ ዝናብ ባለመኖሩ ከፍተኛ የሆነ የቤት እንስሳት ሞት መኖሩን የሱማሌ ብሔራዊ ክልል አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን ኃላፊ በሽር አረብ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አክለውም፣ እስካሁንም አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት ማለቃቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ የድርቁ ሁኔታ ምንም ዓይነት መሻሻል እያሳየ አይደለም ብለዋል።
ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ የሞቱት እንሰሳት 57 ሺሕ 731 ግመሎች፣ 328 ሺሕ 447 በጎች፣ 655 ሺሕ 951 ፍየሎች፣ እንዲሁም ከ37 ሺሕ በላይ አህዮች፣ በጥቅሉ ከአንድ ሚሊዮን 121 ሺሕ 762 በላይ የቤት እንስሳት መሆናቸውን ኃላፊው አብራርተዋል። በበረሃማ አካባቢዎች መረጃ ያልሰጡ አርብቶ አደሮች በመኖራቸው የሞቱት የቤት እንስሳት ቁጥር ከዚህም የላቀ እንደሚሆን ነው ያብራሩት።