አዲስ አበባ የነዋሪ ቁጥርና የፖሊስ ኃይል ምጥጥን ለማስተካከል፣ የከተማዋን ፖሊስ ቁጥር ወደ 50 ሺሕ ለማሳደግ በሁሉም ክልሎች መልማዮች ተልከዋል

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶችን ቁጥር 50 ሺሕ ለማድረስ ታቀደየአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን በከተማ ውስጥ ያለውን የነዋሪ ቁጥርና የፖሊስ ኃይል ምጥጥን ለማስተካከል፣ የከተማዋን ፖሊስ ቁጥር ወደ 50 ሺሕ ለማሳደግ መታቀዱን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ የፖሊስ ኃይሉን ቁጥር ለማሳደግ ተከታታይ ምልመላ እንደሚያደርግ አስታውቆ፣ በዚህ ዓመትም ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መልማዮችን መላኩን ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ የነዋሪዎቿ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረና አሁን ላይ 6.8 ሚሊዮን ነዋሪዎች እንደሚገኙባት አስታውቋል፡፡ ይሁንና በከተማ ውስጥ ያለው የፖሊስ ኃይል ይህንን የሕዝብ ቁጥር የማይመጥንና የብዙዎቹን የከተማዋን አከባቢዎች የማይሸፍን መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተደዳሩ ያደረገው ጥናት እንደሚያመላክተው፣ በከተማዋ ውስጥ ያለው የፖሊስ ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ምጣኔ በሁለት እጥፍ ያነሰ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አንድ የፖሊስ አባል እየሸፈነ ያለው ቢያንስ የአራት ፖሊሶችን ተግባርና ኃላፊነት ነው፡፡

እንደ ኮማንደር ፋሲካ ገለጻ፣ የፖሊስ ቁጥሩ ከነዋሪው ብዛት ጋር ካለመመጣጠኑም ባሻገር፣ በከተማዋ 11 ክፍላተ ከተማዎች ከሚገኙ 121 ወረዳዎች ውስጥ፣ የፖሊስ ጣቢያዎች ያሉት በ72 ያህሉ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በቀሪዎቹ ወረዳዎች ላይ አዳዲስ የፖሊስ ጣቢያዎችን ለመክፈት እየተሠራ መሆኑን ተናግረው፣ ጣቢያዎቹን ለመክፈት የሰው ኃይል፣ የቢሮና የቁሳቁስ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ኮማንደር ፋሲካ የከተማዋ ስፋትና የነዋሪው ብዛት በፍጥነት እየጨመረ መሆኑንና ችግሩን ለመቅረፍ፣ “አንድ ፖሊስ ስንት ሰዎችን መጠበቅ አለበት?” የሚለው ሳይንሳዊና ዓለም አቀፋዊ ደረጃዎችን መሠረት በማድረግ እየተሠራበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረት ኮሚሽኑ ቢያንስ በአምስት ዓመት ውስጥ የአዲስ አበባ ፖሊስን ቁጥር 50 ሺሕ ለማድረስ ማቀዱን አስታውቀዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም. የሦስት ሺሕ ፖሊሶችን ቅጥር የፈጸመው የፖሊስ ኮሚሽኑ፣ በአሁኑ ጊዜ ምልምል ፖሊሶችን በኮልፌ ፖሊስ አካዳሚ እያሠለጠነ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዙር ምን ያህል ፖሊሶች ለመቅጠር እንደታሰበ ባይናገሩም፣ ምልመላው የሚካሄደው ከተማዋ የሚያስፈልጋትን 50 ሺሕ ፖሊሶች ለማሟላት በተያዘው ዕቅድ መሠረት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ኮማንደር ፋሲካ እንደሚያስረዱት፣ አዳዲስ ፖሊሶችን ለመመልመል ሥልጠና የተሰጣቸው የፖሊስ አመራሮች፣ ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደሮች ወደሚገኙ ዋና ከተሞች፣ እንዲሁም ሕዝብ በብዛት ይገኝባቸዋል የተባሉ አከባቢዎች ተሰማርተዋል፡፡

ለምልመላ የተላኩት የፖሊስ አመራሮች በተያዘው መጋቢት ወር አጋማሽ ምልመላውን ጨርሰው ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ተመልማዮቹ ቀጥታ ወደ ሥልጠና እንደሚገቡም አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትን በሁሉም ክልሎች የመመልመል ሥራ አዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት በመሆኗና ሁሉንም አከባቢ ያማከለ የሰው ኃይል ያስፈልጋታል የሚለው በመታመኑ፣ ሒደቱ ከዚህም ቀደምም ሲሠራበት እንደቆየ ኮማንደር ፋሲካ አስረድተዋል፡፡

ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማቶቿ ተጠሪነት ወደ ፌደራሉ መንግሥት የተዛወረባት አዲስ አበባ፣ ፖሊስ ኮሚሽኗም ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ነው፡፡

በ1996 ዓ.ም. የወጣው የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ አንቀጽ 14፣ ከአሥር በላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አዋጅ አንቀጾችና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መተዳደሪያ ደንብ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ላይ ተፈጻሚነት እንዳላቸው ደንግጓል፡፡ በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ፖሊስ ምልመላ የሚካሄደው የፌደራል ፖሊስን የምልመላ ሥርዓት ተከትሎ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም በ2005 ዓ.ም. የወጣው የፌደራል ፖሊስ አባላት መተዳደሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ አንቀጽ አራት ንዑስ አንቀጽ ሦስት፣ የፖሊስ አባላት ምልመላ የአገሪቱን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ እንዲሁም የፆታ ተዋጽኦ ያገናዘበ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2004 ዓ.ም. አንስቶ በአዋጅ ወደ ፌደራል ፖሊስ የዞረውን የከተማዋ ፖሊስ ተጠሪነት ወደ ከተማ አስተዳደሩ መመለስ ይፈልጋል፡፡ ይኼንን ለማድረግ መነሻ የሚሆኑ ምክንያቶችን አጥንቶ ለፌደራሉ መንግሥት በማቅረብ ንግግር እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የፖሊስ ኮሚሽኑን ተጠሪነት ወደ ራሱ ለማዞር የሚያስችሉ ሕጋዊ ማዕቀፎች እንዳሉት ገልጾ፣ አንድ ተቋም ለሁለት አካል ማለትም ለፌደራሉ መንግሥትና ለከተማ አስተዳደሩ ተጠሪ መሆኑ በራሱ ችግር መፍጠሩን አስታውቋል፡፡

በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመጀመሪያ መደበኛ ጉባዔ ላይ ስለኮሚሽኑ ተጠሪነት ጉዳይ አበክረው የተናገሩት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣  የከተማዋ ፖሊስ ተቋማዊ ሪፎርም እንደሚያስፈልገውና ከተማዋም ራሱን የቻለ ጠንካራ ፖሊስ እንደሚገባት ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከሌሎች ፖሊስ ተቋማት ጋር መወዳደር እንኳን እንደማይችል የተናገሩት ከንቲባዋ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ በሎጂስቲክስ፣ በቁጥር፣ በብቃትና በሥነ ምግባር ሪፎርም መደረግ እንደሚገባው አውስተዋል፡፡ የከተማዋ ፖሊስ ራሱን የቻለ የአቅም መገንቢያ ኮሌጅና ማሠልጠኛ ማዕከል እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር