በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሆሳዕና ከተማ በሚገኘው ዋቻሞ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ ተማሪዎች 126ኛውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ማክበራቸውን ተከትሎ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ተማሪዎቹ፣ ድሉን የሚያወሳ ልብስ (ቲሸርት) ለብሰን በከተማዋ የካቲት 23/2014 የዓድዋን ድል ከሕዝቡ ጋር በማክበራችን የተነሳ ነው ጥቃት የተከፈተብን ያሉ ሲሆን፣ ጥቃት የደረሰባቸው ግን በማግስቱ ሐሙስ የካቲት 24/2014 መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም፣ በዕለቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከጥቃት ሸሽተው ከዩኒቨርስቲው ውጭ እንደነበሩ እና በእግራቸው 20 ኪሎ ሜትር ተጉዘው በአንድ የገጠር ቤተክርስቲያን ተጠልለው መቆየታቸውን ገልጸዋል። የካቲት 24/2014 የክልሉ የጸጥታ አካላት ወደ ዩኒቨርስቲው እንዲመለሱ ቢያስገድዷቸውም፣ ለደኅንነታቸው በመሥጋት በቤተክርስቲያን ማደራቸውን ገልጸዋል። ሌሎች ተማሪዎችም እንዲሁ በሌላ ቦታ ተጠልለው እንደነበርና ቀኑን ሙሉ ምግብ እንዳላገኙ ነው የገለጹት። ከጥቃቱ ማምለጥ ያልቻሉ ተማሪዎች በተለይም ደግሞ ሴቶች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው እና በዚህም ጉዳት የደረሰባቸው ከ200 ያላነሱ ተማሪዎች ሆስፒታል ሳይገቡ እንዳልቀረ ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ ጥቃት የተፈጸመባቸው በዩኒቨርስቲው ባሉ ሌሎች ተማሪዎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላት መሆኑንም ነው የገለጹት። ጥቃቱም ማንነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን አንስተዋል። የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላቱ፣ ለብሰውት የነበረውን ስለዓድዋ ድል የሚያወሳ ቲሸርት አስወልቀው የገረፏቸው ተማሪዎች እንዳሉም ገልጸዋል።
ተማሪዎች በተደጋጋሚ የጸጥታ ሥጋቶች መኖራቸውን እና ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያደርግ አስተማማኝ መፍትሔ እየተወሰደ አይደለም ሲሉ ይገልጻሉ። በአንድ የትምህርት ዘመን ብቻ ኹለት ጊዜ በዩኒቨርስቲው ውስጥ ረብሻ መከሠቱ እና በተመራቂዎች ላይ የአካልና የሥነ-ልቦና ጉዳት መድረሱ ተመላክቷል።
የዋቻሞ ዩኒቨርስቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዳንኤል ጋዴ፣ ተማሪዎች እርስ በርስ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ግጭት ፈጥረው ነበር ሲሉ ስለጉዳዩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ግጭቱ የከፋ ጉዳት አላስከተለም ያሉት ኃላፊው፣ የተወሠኑ ተማሪዎች ግን መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውና ሆስፒታል ገብተው ታክመው ወደ ማደሪያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል። ኾኖም ግን ምን ያህል ተማሪዎች ወደ ሆስፒታል እንደገቡ እና የደረሰባቸውን የጉዳት መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ኃላፊው ዩኒቨርስቲውን ለቀው የወጡ ተማሪዎች መኖራቸውንም ጠቅሰው፣ ተወያይተው ወደ ግቢው የሚመለሱ መሆኑን አንስተዋል። ኃላፊው አክለውም፣ አጀንዳ ያላቸው አካላት ናቸው ችግሩን የሚያባብሱት ካሉ በኃላ፣ በዕለቱ ተማሪዎች መደበኛ ሥራቸውን እየሠሩ እና በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ በነጻነት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርስቲው በቅርብ ዕርቀት እየተከታተለ ተማሪዎቹን እያወያያ ነው ያሉት ኃላፊው፣ የግጭቱ መነሻ ምን እንደሆነ እና ጥቃቱን የፈፀሙት ተማሪዎች ናቸው ወይስ የጸጥታ ኃይሎች የሚለው በመጣራት ላይ ነው ብለዋል።
ኾኖም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ባለው ጊዜ በርካታ ተማሪዎች ቤተክርስቲያን ተጠልለው እንደሚገኙና ለደኅንነታቸው አስጊ በሆነ ኹኔታ ውስጥ እንዳሉ ገልጸዋል። ወደ ዩኒቨርስቲው ብንገባም ባልታሰበ ጊዜ ጥቃት ሊደርስብን ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ተማሪዎቹ ተናግረዋል።