“በሀገራችን የተፈጠረው የወንድማማቾች ግጭት ሁሉን ያዳረሰ ቢሆንም ቤተክርስቲያን ይበልጥ ተጎድታለች አብያተ ክርስቲያናት ተደፍረዋል ምዕመናን ተጎድተዋል” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

(ተሚማ/አዲስ አበባ) – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በዛሬው ዕለት 9ኛ ዓመት የፓትርያርክነት በዓለ ሢመታቸው በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ቅዱስነታቸው አርሶ ማምረት ነግዶ ማትረፍ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው ያሉ ሲሆን የኛ ሥራ ከሰላም ጋር የተመሠረተ እንደሆነ መፅሐፍ ይናገራል በማለት ሰላም በሰዎች ድርጊት ሊገኝና ሊጠፋ የሚችል ነገር ነው
ይሁንና የሰላምን ተልዕኮ እየተወጣን ነው ወይ የሚለውን ለህሊናችን እንተወው ፤ እያንዳንዷ ንግግራችን በቃለ ወንጌል የተቃኘች እንድትሆን አደራ እንላለን በማለት ገልፀዋል።

እኛ ካህናት የሰላም ጠባቂ ሆነን ተሹመናል ነገር ግን ሰላምን ጠብቀን እያስጠበቅን ነው ወይ ? ይሄ የወቅቱ ዓቢይ ጥያቄ ነው በማለት ጠይቀዋል ፤ከእግዚአብሔር ኃላፊነት የተቀበልነው ሁሉንም እኩል እንድናይና እንድናገለግል ነው ያሉህ ቅዱስ ፓትርያርኩ በልዩ ምክንያት ፀብ ሲነሳ መሀል ሆነን ልንገላግል ይገባል አንዱን ደግፈን አንዱን ገሸሽ ማድረግ በእግዚአብሔር ዘንድ ያስጠይቀናል ። ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ካህናት ያላት ቤተክርስቲያን ሀገር ውስጥ ሰላም ጠፋ ማለት ሥራችንን እየሰራን እንዳልሆነ ማሳያ ነው።

ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል ሁሉም ታሪክ ጥሎ ያልፋል ታሪክን መሸፋፈን አንችልም። ትኩረታችን ታሪክን መደበቅ ሳይሆን ታሪክን ማሳመር ሊሆን ይገባል። ቤተክርስቲያናችን ዛሬ ከውስጥም ከውጪም እየተፈተነች ነው። ከመሬት ተነስቶ ጳጳስ ነኝ ፓትርያርክ ነኝ የሚሉ ህገ ወጦች ተበራክተዋል።
ለዚህ ሁሉ መፍትሄው ምን ይሆን ? ማውገዝ ነው ማሳደድ ነው ወይስ ዝም ማለት? ከአንድም ሁለት ሦስቴ መክሮ አስመክሮ እንቢ ካለ ማውገዝ መፍትሄ ነው ሆኖም ግን የንስሐ ጊዜ መስጠት ተገቢ ነው። ከሁሉም በፊት ግን ችግሮችን በመወያየትና በመነጋገር መፍታት ተገቢ ነው ብለዋል ቅዱስነታቸው።

በሀገራችን የተፈጠረው የወንድማማቾች ግጭት ሁሉን ያዳረሰ ቢሆንም ቤተክርስቲያን ይበልጥ ተጎድታለች አብያተ ክርስቲያናት ተደፍረዋል ምዕመናን ተጎድተዋል። ለሀገር ሰላም ይመጣ ዘንድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል ከግጭት የሚገኝ ትርፍ የለም ምርጫችን ሰላም እና ሰላም ብቻ ይሆን ዘንድ እንመክራለን። በግጭቱ እየተሳተፉ ያሉት የቤተክርስቲያን ልጆቻችን ናቸው። የቤተክርስቲያንን ልዕልና እንዳናስነካ እንዳናስነቅፋት አባታዊ ምክር እናስተላልፋለን ሲል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ።