መንግስት የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመርን ለመሸጥ ከአውሮፓ ኩባንያዎች ጋር እየተነጋገረ ነው።

መንግስት ኢኮኖሚውን ለማሻሻል እና የግሉ ሴክተርን ሚና ለማስፋት በያዘው እቅድ መሰረት የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመርን ወደ ግል ለማዛወር ከአውሮፓ ኩባንያዎች ጋር እየተነጋገረ ነው።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የባቡር መስመሩ ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት እንዲገባና ቀልጣፋ ለማድረግ ተጨማሪ 800 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ያስፈልገዋል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ ግል ለማዘዋወር ከታቀዱ ዋና ዋና የመንግስት ኢንተርፕራይዞች አንዱ ነው። የፕራይቬታይዜሽን ሒደቱን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ገና ይፋ አልሆነም።
በኮርፖሬሽኑ ተቀጥሮ የባቡር ሀዲዱን የሚያስተዳድረውን የቻይና ኩባንያዎች የተወሰነ ድርሻ እንዲኖራቸው ብንጠይቅም ፍቃደኛ አልሆኑም ያሉት የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ወቶበት የተገነባው የባቡር ሀዲድ የኢንቨስትመንት ወጪው ብዙ በመሆኑ ያንን ያህል ገንዘብ የሚያወጣ ካምፓኒ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንዳሉት መንግስት የባቡር መሰረተ ልማቶችን ለማሻሻል ካቀዳቸው እቅዶች መካከል የግሉ ዘርፍ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ አንዱ ነው ።