በኢትዮጵያ ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ዙሪያ ብሔራዊ ምርመራ ሊካሄድ ነው

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ዙሪያ የመጀመሪያ ነው ያለውን ብሔራዊ ምርመራ ሊካሄድ መሆኑን አስታወቀ።

ብሄራዊ ምርመራው የመጀመሪያ እንደሆነ የተናገሩት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ስልታዊና ውስብስብ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር ያግዛል ብለዋል።

የብሄራዊ ምርመራው ተልዕኮ የህግ የበላይነትን በማስፈን ፍትህን በማረጋገጥ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃና አከባበርን ማጎልበት ነው ተብሏል።

ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ብሔራዊ ምርመራውን ለማካሄድ የተቀረፀው ፕሮጀክት 15 ሚሊዮን ዩሮ ወጭ የሚደረግበት እንደሆነ እና ድጋፉ ከአውሮፓ ህብረት መገኘቱን መናገራቸውን ኢብኮ ዘግቧል።

ኮሚሽኑ በማረሚያ ቤቶች፣ በፖሊስ ጣቢያዎችና በእገታ ሥር ያሉ ሰዎችን ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የመጎብኘት መብት እንዳለውም ተገልጿል።