ብሔራዊ ታሪካችንን ረስተን ሰባራ ዕቃ እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገባል። – ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ጎለጎታ መዝገበ ምሕረት ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የልደተ ስምዖን በዓል ላይ ያስተላለፉት አባታዊ መልዕክት።
ኢትዮጵያ ሀገራችን የአየር ንብረቷ ብቻ ተወዳጅ ነው። በዚህና በሌላም ምክንያት አልሳካ ብሎ እንጅ ይችን ሀገር ለመውረስ የማይጎመጅ የለም። እስከ አሁን ድረስ የቆየነው በአባቶቻችን ጥንካሬ ነው። አሁን እንደ ጥንት አባት እናቶቻችን ጠንካራ አይደለንም። እምነቱም መተማመኑም የለም፤ ፍቅሩም፣ መተሳሰቡም የለም፤ ፍቅር ከሌለ ሁሉም ነገር የለም። ከብሔራዊ ታሪካችን አንዱ መተማመን፣ መፈቃቀር፣ መደማመጥ፣ መከባበር፣ እግዚአብሔር መፍራትን ያካትታል። ይህን የመሳሰለው የብሔራዊ ታሪካችን፣ እምነታችን፣ የመልካም ባህላችንና እሴታችን አካል እየተረሳ ነው።
ብሔራዊ ክብራችንንና ታሪካችንን ረስተን ሰባራ ዕቃ እንዳንሆን ሁላችንም ልንጠነቀቅ ይገባል። የእኛን አኩሪ ታሪክ ትተን የሌላውን መቀላወጥ ክብር አይሰጥም ብለዋል ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በመልእክታቸው ።
ካህናት የንሰሀ ልጆቻችሁን በደንብ አድርጋችሁ ማስተማር ያስፈልጋል። በስነ-ምግባር የበቁ፣ ችግር ፈች እንጂ ችግር ፈጣሪ እንዳይሆኑ፤ ዜጎች ብሔራዊ ጀግኖቹን በትክክል አውቆ ተገቢውን ክብር እንዲሰጥ እንዲንከባከብ ማድረግ ያስፈልጋል። ሰው ብቻ አይደለም ብሔራዊ ጀግና ማለት። የተቋምም ብሔራዊ ጀግና አለ። ሩቅ መሄድ አያስፈልግም ወልድያ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው። በክፉ ቀን ጀግና የሆኑ የቤተ እምነት እና የባህላዊ ተቋማት አሉ። በእነዚህ ተቋሞች ስር ነው የሚያረጋጉ፣ የክፉ ቀን ደራሽ እውነተኛ አባቶች የተገኙት። ጊዜም፣ ጉልበትም፣ ገንዘብም ተዳምሮ በክፉው ጊዜ፤ በአስቸጋሪ ወቅት መልካም ስራ መስራት ይበልጥ በፈጣሪም ዘንድ ዋጋ እንደሚያሰጥ የተረዱ አባቶች ወልድያ ላይ በተግባር አይታችኋል።
በየጊዜው፣ በየዕለቱ የምንሰማው ለጆሮ የሚከብድ በመንግሥትም የሚነገረው ይህን ያህል ተፈናቀለ፣ ይህን ያህል ሞተ ነው። እግዚአብሔር ይህን ያህል ሞተ ይህን ያህል ተፈናቀለ ሳይሆን፤ ይህን ያህል ዜጋ ለማፈናቀል፣ ለመግደል ያቀደን አካል ያሰበውን ክፉ ሀሳብ ሳያሳካ የዜጎቼን ሕይወት ደህንነት በፍጥነት አስጠበኩ የሚል ዜና ያሰማን ዘንድ በዓቢይ ጾም ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ሲል የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል ።
May be an image of 3 people, people standing and outdoors