እስራኤል የአፍሪካ ኅብረት የታዛቢነት መቀመጫ ጥያቄ የመሪዎቹ ጉባዔ እንዲያጸድቀው ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

May be an image of one or more people and indoorበአዲስ አበባ ትናንት እና ዛሬ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጉባዔ እስራዔል በኅብረቱ ባላት የታዛቢነት መቀመጫ እና የዲፕሎማሲ ውክልና ላይ የመወያየቱን እና ድምጽ የመስጠቱን ሃሳብ ወደ ቀጣዩ ዓመት እንዳስተላለፈው ዓለማቀፍ ዜና ወኪሎች ዘግበዋል። የመሪዎቹ ጉባዔ ድምጽ በመስጠት ፋንታ ጉዳዩን እንደገና አጥንቶ ለቀጣዩ ዓመት የኅብረቱ መሪዎች ጉባዔ የውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ አቋቁሟል።

የኅብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ እስራዔል በኅብረቱ የታዛቢነት መቀመጫ እና የዲፕሎማሲ ውክልና እንዲሰጣት ያቀረበችውን ጥያቄ፣ ለሰላም ጠቃሚ ርምጃ መሆኑን በመጥቀስ የተቀበሉት ባለፈው ሐምሌ ነበር። ፋኪ ለእስራኤል የታዛቢነት መቀመጫ መፍቀዳቸውን ተከትሎ፣ በተለይ ደቡብ አፍሪካ እና አልጀሪያ ውሳኔውን ክፉኛ በማውገዝ የኅብረቱ መሪዎች ጉባዔ የእስራዔልን የታዛቢነት መቀመጫ እንዲሰርዝ ሲወተውቱ ቆይተዋል። በተመሳሳይ በኅብረቱ የታዛቢነት መቀመጫ ያላት ፍልስጤም እስራዔል ባሁኑ ወቅት በፍልስጤማዊያን ላይ የአፓርታይድ ሥርዓት እንደዘረጋች እና በፍልስጤማዊያን መከራ እና ግፍ እየፈጸመች መሆኗን በመጥቀስ የኅብረቱ መሪዎች የእስራዔልን የታዛቢነት መቀመጫ እንዲሰርዝ ትናንት በጠቅላይ ሚንስትሯ በኩል ጉባዔውን ጠይቃ ነበር። እስራዔልም በፊናዋ የኅብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ያጸደቁላትን የታዛቢነት መቀመጫ ጥያቄ የመሪዎቹ ጉባዔ ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያጸድቀው ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

የመሪዎቹ ጉባዔ ጉዳዩን እንደገና አጥንቶ ለቀጣዩ ዓመት የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ያቋቋመው ኮሚቴ ደቡብ አፍሪካን፣ አልጀሪያን፣ ሩዋንዳን፣ ናይጀሪያን፣ ዲሞክራሲያዊት ኮንጎ ሪፐብሊክን እና ካሚሮንን ያቀፈ ነው። ዲፕሎማቶች እና ታዛቢዎች የመሪዎቹ ጉባዔ በጉዳዩ ላይ ድምጽ ከሰጠ፣ የኅብረቱ አባል ሀገራት ከሁለት ተቃራኒ ጎራ ሊከፈሉ ይችላሉ የሚል ስጋት ነበራቸው። የመሪዎቹ ጉባዔ የኮሚሽነር ፋኪን ውሳኔ መቀልበስ የሚችለው በ2/3ኛ ድምጽ ብቻ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]