ለሕዳሴ ግድቡ ዘንድሮ የተሰበሰበው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ660 ሚሊዮን ብር ቀነሰ

አዲስ ማለዳ -ባለፉት ስድስት ወራት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ 539.5 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በ2014 ስድስት ወራት ውስጥ የተሰበሰበው ገንዘብ በ2013 ተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው ጋር ሲነጻጸር በ660 ሚሊዮን ብር ቅናሽ ማሳየቱ ተገለጸ።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሐምሌ ወር 2013 ጀምሮ እስከ ባለፈው ታኅሣሥ 30/2014 ድረስ፣ የተለያዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገዶችን በመጠቀም 539 ሚሊዮን 583 ሺሕ 435 ብር ገቢ እንደተሰበሰበ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

ባለፈው ዓመት ከሐምሌ 1/2012 እስከ ታኅሣሥ 30/2013 የተሰበሰበው ገንዘብ 1.2 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ስድስት ወር ጊዜ የተሰበሰበው ገንዘብ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም በ660 ሚሊዮን 416 ሺሕ ብር በላይ ቅናሽ ማሳየቱ ነው የተነገረው።

ይህም የሆነበት ምክንያት ባለው አገራዊ ኹኔታ ከአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ጋር ተያይዞ የተለያዩ መድረኮችን እና ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎችን እንደልብ መሥራት ባለመቻሉ እንደሆነ ተነስቷል። እንዲሁም በባለፈው ዓመት አዲስ አበባ ላይ የሕዳሴ ግድቡ ዋንጫ ስለነበር ከሌሎች ዓመታት ኹሉ የተለየ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ነው የተገለጸው።

ከሐምሌ 1/2013 እስከ ታኅሣሥ 30/2014 ከተሰበሰበው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ፣ 216 ሚሊዮን 694 ሺሕ 930 የሚሆነው ብር ከአገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ የተገኘ መሆኑ ተመላክቷል። እንዲሁም፣ ከዳያስፖራ ቦንድ ሽያጭ እና ስጦታ 204 ሚሊዮን ብር 63 ሺሕ 676 ብር፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስጦታ አካውንት ገቢ የሆነ 6 ሚሊዮን 560 ሺህ 501 ብር የተሰበሰበ ሲሆን፣ በተጨማሪም ከ‹ፒን› ሽያጭ ገቢ 86 ሺሕ 900 ብር እና ከ8100 አጭር የሞባይል የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት 88 ሚሊዮን 177 ሺሕ 725 ብር የተገኘ መሆኑን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሚዲያ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሀይሉ አብርሃም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አያይዘውም፣ ባለፈው ታኅሣሥ ወር ብቻ 44 ሚሊዮን 638 ሺሕ 937 ብር ገቢ ለግድቡ እንደተሰበሰበ አሳውቀዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፣ በአሁኑ ወቅትም የግድቡን የሙከራ ሥራ ምክንያት በማድረግ ገቢ የመሰብሰብ ሐሳብ የነበረ ቢሆንም፣ ግድቡ ወደ መጠናቀቁ እያመራ በመሆኑ ካለው ወቅታዊ ኹኔታና ከተለያዩ ነገሮች አንጻር ጉዳዩን ማራገብ አስፈላጊ ሆኖ ባለመገኘቱ ሥራው በዝምታ እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ግድቡ ከተጀመረበት 2003 ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 30/2014 ድረስ ባለው ጊዜ፣ በአጠቃላይ ከአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ከሚገኝ ገቢ፣ ከዳያስፖራ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች የተሰበሰበ ገቢ ሲጠቃለል፣ የአገር ውስጥ ቦንድ ግዥና ልገሳ 14 ቢሊዮን 439 ሚሊዮን 664 ሺሕ 982 ብር መሆኑ ተመለክቷል። ከዳያስፖራ ቦንድ ግዥና ልገሳ እንዲሁ 1 ቢሊዮን 356 ሚሊዮን 956 ሺሕ 99 ብር የተገኘ ሲሆን፣ ከልዩ ልዩ ገቢዎችም 471 ሚሊዮን 977 ሺሕ 29 ብር መገኘቱን ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በዚህም፣ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ እስከ ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ድረስ 16 ቢሊዮን 268 ሚሊዮን 598 ሺሕ 110 ብር ከ57 ሳንቲም መሰብሰቡ ተመላክቷል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የግንባታ ሥራው 84.28 በመቶ መድረሱንም ለማወቅ ተችሏል።