ከደረታቸው በታች በምዕራብ ሐረርጌ ተጣብቀው የተወለዱት ሕጻናት ለከፍተኛ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ ተላኩ።

ተጣብቀው የተወለዱት ህጻናትበኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሂርና ከተማ ከደረታቸው በታች ተጣብቀው የተወለዱት ሕጻናት ለከፍተኛ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ ተላኩ።

ረቡዕ ጥር 25/2014 በሂርና ሆስፒታል የተወለዱት ሕጻናት “ከደረታቸው በላይ ሁለት ሰው፤ ከደረታቸው በታች ደግሞ የአንድ ሰው አካል ይዘው ነው የተወለዱት” ሲሉ የሂርና ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ፋሚ መሐመድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከደረታቸው በታች የአንድ ሰው አካል ያላቸው ሕጻናቱ፤ የመጸዳጃ ቀዳዳ ስለሌላቸው “ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ጭሮ ሆስፒታል እንዲያመሩ በመወሰን ሪፍር አድርገናል” ብለዋል ዶ/ር ፋሚ።

ነገር ግን የጭሮ ሆስፒታልም ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ሪፍር በመጻፉ ተጣብቀው የተወለዱት ጨቅላዎች ወደ አዲስ አበባ ሊጓዙ መሆኑን የጨቅላዎቹ ወላጅ አቶ በትራ ሉሉ ሐሙስ ጥር 26/ 2014 ዓ.ም. ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከወሊድ በፊት

ነዋሪነታቸው በምዕራብ ሐረርጌ ጡሎ ወረዳ ኢባስ ቀበሌ ውስጥ የነበሩት የጨቅላዎቹ ወላጆች፤ ከወሊድ ሁለት በፊት በተደረገ ምርመራ እርግዝናው መንታ ልጆች እንደሆነ ከባለሙያዎች ተነግሯቸው ነበረ።

እናቲቱ ከመውለዷ ከሁለት ወራት በፊት ለእርግዝና ክትልል ወደ ሂርና ሆስፒታል መጥታ እንደነበረ የሂርና ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ፋሚ መሐመድ ያስታውሳሉ።

“ነፍሰ ጡር እናቶች በመደበኛነት ወደ ጤና ተቋም እየመጡ ክትትል ማድረግ አለባቸው። ይህች እናት ግን ነብሰ ጡር በነበረችበት ጊዜ ሙሉ ክትትል አላደረገችም። ከሁለት ወራት በፊት ነበር እዚህ መጥታ የታየችው” ይላሉ ሜዲካል ዳይሬክተሯ።

በሂርና ሆስፒታል በነበራት ምርመራ መንታ ልጆችን እንደጸነሰች ተገምቶ ነበር። ይሁን እንጂ “ምጧ መጥቶ እንድትወልድ ሲደረግ የመጀመሪያው ልጅ ከሁለተኛው ጋር ተጣብቆ ወጣ” በማለት በወሊድ ወቅት የጤና ባለሙያዎች ያልጠበቁት እንዳጋጠማቸው ሜዲካል ዳይሬክቷ ዶ/ር ፋሚ ያስረዳሉ።

ተጣብቀው የተወለዱት ህጻናት “ጾታቸው ወንድ ነው። ያላቸው ብልትም አንድ ነው። ሁለት እግር ነው ያላቸው። ከደረታቸው በላይ ግን የሁለት ሰው አካል ነው ያላቸው” በማለት ከወሊድ በኋላ የተመለከቱትን ገልጸዋል።

ጨቅላዎቹ ከተወለዱበት ሂርና ሆስፒታል ወደ ጭሮ ሆስፒታል እስከተላኩበት ሰዓት ድረስ የጤንነት ሁኔታቸው መልካም እንደነበረ ተናግረው፤ ሁለቱም ጭቅላዎች ጡት ይጠቡ እንደነበረም ሜዲካል ዳይሬክተሯ ለቢቢሲ ተናግረዋል።