በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው ችግር የሚገባውን ትኩረት ሳያገኝ እንደቀጠለ ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት የምዕራብ ኦሮሚያ ክፍል ሰዎች በግፍ የሚገደሉበት፣ የሚፈናቀሉበት እና ንብረት የሚወድምበት አካባቢ ሆኖ እስካሁን ቀጥሏል። በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች፣ አስተዳዳሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎችም የጥቃቶቹ ሰለባዎች ሆነዋል። በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው ችግር በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄድ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት የሚገባውን ትኩረት ሳያገኝ እንደቀጠለ ነው።

BBC Amharic : በ2013 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ በተከታታይ ለቀናት በተፈጸሙ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በታጣቂዎች መገደላቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ነቀምት የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ ናትከዚህ ጥቃት በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች፣ አስተዳዳሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና ሌሎችም የጥቃቶቹ ሰለባዎች ሆነዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ ዞኖች ውስጥ የሚፈጸሙት ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች እና ዝርፊያዎች በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄድ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት የሚገባውን ትኩረት ሳያገኝ እንደቀጠለ ነው።

መልኩን እየቀያየር የሚያጋጥመው ጥቃት ለበርካታ ዓመታት በሰላም አብሮ ሲኖር የነበረን ማኅበረሰብ በዓይነ ቁራኛ እንዲተያይ ምክንያት እየሆነ ነው። ከትግራዩ ጦርነት በፊት የጀመረው በአካባቢው ያለው የሰላም መደፍረስ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

ለመሆኑ ቀደም ሲል በሰላማዊነቱ የሚታወቀው የምዕራብ የኦሮሚያው ክፍል ወለጋን መረጋጋት እንዲርቃትና በርካቶችን ሰለባ እንዲሆኑ ያደረጉት ጥቃቶች እንዲቀጥሉ ያደረጉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? አምስቱ ዋነኛ ምክንያቶችን እነሆ።

Presentational grey line

የታጣቂዎች እንቅስቃሴ

መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለውን እና እራሱን ‘የኦሮሞ ነጻነት ጦር’ ብሎ የሚጠራው ቡድን በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ በስፋት በመንቀሳቀስ ለክልሉ እና ለፌደራል መንግሥት ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

‘ሸኔ’ ወይም ‘የኦሮሞ ነጻነት ጦር’ የሚንቀሳቀስባቸው ስፍራዎች የደኅንነት እጦት ያጋጠማቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች ሆነዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት ይህ ቡድን ተጠያቂ በሆነበትና በካማሺ ዞን አስተዳዳሪዎች ላይ የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ ከ100 ሺህ በላይ ሕዝብ ከመኖሪያው እንዲፈናቀል እና በርካቶች በጥቃቱ እንዲገደሉ ምክንያት ሆኖ ነበር።

የሸኔ ወይም የኦሮሞ ነጻነት ጦር በጀምላ ግድያ፣ ዘረፋ፣ በንጹሃን እና በመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ፣ መንገድ በመዝጋት፣ የሕዝብ እና የመንግሥት ንብረት በማውደም፣ ሰዎችን አፍኖ በመውሰድ እና በሌሎች ወንጀሎችም ይከሰሳል።

በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ እና ባቦ ጋምቤል ወረዳዎች እንዲሁም በሆሮ ጉዱሩ ዞን አቤ ዶንጎሮ፣ አሙሩ እና አባያ ጮመን ግፍ ከተፈጸመባቸው ወረዳዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

በተመሳሳይ በተቀሩት ሁለት የወለጋ ዞኖች፤ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እና ምሥራቅ ወለጋ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ወንጀሎች ተፈጽመዋል።

ሰኔ 2013 ዓ.ም. በኪራሙ በተፈጸመው እና ከ100 በላይ ሰዎች ከተገደሉበት ጥቃት በሕይወት መትረፍ የቻለው አርሶ አደር ለቢቢሲ እንደተናገረው በአሁኑ ወቅት በሽሽት በአማራ ክልል ውስጥ ይገኛል።

ለደኅንነቱ ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው ይህ አርሶ አደር ትውልድ እና አድገቱ ወለጋ ውስጥ መሆኑን በመናገር በአካባቢው ለተፈጠረው የሰላም እጦት ዋነኛው ምክንያት ‘የሸኔ’ ታጣቂዎች ናቸው ይላል።

“ይሄን ሁሉ የሚያደርገው ሸኔ ነው። ኦነግ ሸኔ ነው ይህን ችግር ያመጣው እንጂ እኛማ ተጋብተን፣ ተዛምደን አይደል እንዴት አብረን ስንኖር የነበረው?” በማለት ይናገራል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በምዕራብ ኦሮሚያ ያለውን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት የፖለቲካ ተንታኝም፤ በአካባቢው ያለውን የደኅንነት እጦት ያባባሰው “የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ነው” በማለት ከአርሶ አደሩ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ይሰነዝራሉ።

ጨምረውም “ዘንድሮ ሳይታረሰ የቀረ ሰፊ መሬት አለ” በማለት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአማራ ብሔር ተወላጅ ከአካባቢው ተፈናቅለው መውጣታቸውን ይገራሉ።

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚሰነዘሩት በርካቶቹ የታጣቂዎች ጥቃቶች ኢላማቸውን የሚያደርጉት በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ይሁን እንጂ በጥቃቶቹ ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎችም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል።

መሰል ጥቃቶች የበቀል እርምጃ እንዲወስድም ምክንያት እየሆኑ ነው።

በታጣቂዎች ጥቃት ከወደሙ መኖሪያ ቤቶች መካከል

በታጣቂዎች ጥቃት ከወደሙ መኖሪያ ቤቶች መካከል

የአማራ ታጣቂዎች

በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ጥቃቶች መሰንዘር ከጀመሩ በኋላ የአማራ ታጣቂዎችም በበቀል እርምጃዎችን በመወሰድ መከሰስ ጀምረዋል።

በሁለቱ ዞኖች ውስጥ በደርግ መንግሥት ወቅት የሰፈሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአማራ ብሔር ተወላጆች ይኖራሉ። ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት የኦሮሞ እና የአማራ ብሔር ተወላጆች በሰላም እና በመተጋገዝ ይኖሩ ነበር።

ይሁን እንጂ ከታጣቂዎች እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ብሔር ተወላጆች መካከል ግጭት መከሰት ጀምሯል።

“ከዚህ ቀደም ታጣቂዎች ብዙ ሰው ገድለዋል (የአማራ ብሔር ተወላጆችን)። አሁን ላይ ታጣቂዎች የገደሉትን ለመበቀል ያገኙትን ኦሮሞ በመግደል በቀል እየተወጡ ነው። ‘ትናንት አብሮን የበላው እራሱ ነው ያስገደለን’ ይላሉ። በየቀኑ ሰው እየተገደለ ነው” በማለት የምዕራብ ኦሮሚያን የፀጥታ ሁኔታን በቅርበት የሚከታተሉት ተንታኝ ይናገራሉ።

ታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የአማራ ታጣቂዎች የወሰዱት የበቀል እርምጃ ነው በተባለ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ንብረትም ወድሟል።

በሆሮ ጉዱሩ ዞን፤ የጃርዳጋ ጃርቴ ወረዳ ሃርቡ ነጋሶ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት ግለሰብ በዚህ ጥቃት ንብረታቸው ስለወደመባቸው አካባቢውን ጥለው ተሰደዋል።

“ዘጠኝ ሰዎች ተገድለው ነበር። ሟቾቹ ደግሞ መሸሽ የማይችሉ ሰዎች ናቸው። የ90 ዓመት አዛውንት ከሟቾቹ መካከል ይገኙበታል” በማለት ተፈናቃዩ ይናገራሉ።

ሌላ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አርሶ አደር፤ በሁለቱ ብሔር ተወላጆች መካከል እርቅ ለማውረድ ለውውይት በተቀመጡ ወቅት፤ የአማራ ብሔር ተወላጆች ‘ለደኅንነታችን ሰግተን ፋኖን አስመጥተናል’ ብለው ስለመናገራቸው ይገልጻሉ።

ሌላኛው ንብረታቸው ወድሞ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ እንደሚሉት የአማራ ታጣቂዎች ጥቃት ሲፈጽሙ የቆዩት መንግሥት ሸኔ የሚለው ታጣቂ ቡድን ሲንቀሳቀስ በነበረበት ቦታ ነው ይላሉ።

“ሲንቀሳቀሱ በነበሩት ቦታ ነው ያቃጠሉት። አሁን እነሱ (የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቡድን) በቦታው የሉም። ይህ የብሔር ግጭት ሳይሆን የፖለቲካ መልክ ነው ያለው። በቀል የሚወጡም ይመስላል” በማለት ያስረዳሉ።

የቀድሞው የምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አለማሁ ተስፋ ከዚህ ቀደም ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በአካባቢው ‘በአማራ ታጣቂዎች’ ጥቃት ተፈጽሟል ሲሉ ተናግረው ነበር።

ከዚህ አንጻር ከጥቃቶቹ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ‘የአማራ ታጣቂዎች’ የተባሉትን ሃሳብ አግኝቶ ለማካተት አልተቻለም።

የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር እና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሻፊ ሁሴን በበኩላቸው በቅርብ ጊዜያት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ዒላማ ባደረገው ጥቃት ተሳታፊ የሆኑት በዚያው በክልሉ ውስጥ የሚኖሩት ናቸው ይላሉ።

እንደ ኃላፊው ከሆነ ታጣቂዎቹ የመንግሥት እንቅስቃሴን ተከትለው ከቦታ ቦታ እንደሚንቀሳቀሱ ያስረዳሉ።

መንግሥት

ከመንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነቶች መካከል የዜጎችን ደኅንነት ማረጋገጥ እንዱ ቢሆንም፤ በምዕራብ ኦሮሚያ የሚኖሩ የሁለቱም ብሔር ተወላጆች መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አልቻለም ይላሉ።

“የመንግሥት አካል ሁኔታውን መቆጣጠር ነበረበት። ለጠፋው ሕይወት እና ንብረት መንግሥት ተጠያቂ መሆን አለበት” በማለት የጃርዳጋ ጃርቴ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ይናገራሉ።

ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ ግጭት እየተበራከተ ሲሄድ እንኳን መንግሥት ‘ዝምታን’ መርጧል ይላሉ።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የአስተዳደር እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ግን በዚህ አይስማሙም። አቶ ሻፊ፤ “እንደውም ያለን ኃይል በምዕራብ ነው ያለው። መንግሥት የተለያየ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል” ይላሉ።

በሌላ በኩል በክልሉ መንግሥት ላይ የሚነሳው ቅሬታ፤ አርሶ አደሩ እራሱን ሊከላከል የሚችልበትን ትጥቅ ያስፈታል የሚለው ነው።

በስልጠና ላይ ያሉ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት።

የፎቶው ባለመብት, Oromia Police

የምስሉ መግለጫ, በስልጠና ላይ ያሉ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት።

በአንዳንድ ስፍራዎች መንግሥት ጦር መሳሪያ በታጣቂዎች እጅ ሊገባ ይችላል በሚል ስጋት ነዋሪዎችን ትጥቅ ሲያስፈታ ነበር ተብሏል። አንድ አርሶ አደር “ሸኔን ምክንያት ያደርጋሉ እንጂ እንዴት አንድ ሰው ለሸኔ እንካ ብሎ መሳሪያ ይሰጣል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

አቶ ሻፊ ግን መንግሥት ሚሊሻውንም ሆነ አንድ ወገንን ለይቶ ትጥቅ አያስፈታም ይላሉ።

ይሁን እንጂ በጦር መሳሪያ አማካኝነት ጉዳት እንደሚደርስ ይናገራሉ።

ሌላ መንግሥት ላይ የሚነሳው ትችት፤ የወታደራዊ እርምጃ አማራጭን በመጠቀም በምዕራብ ኦሮሚያ ሰላም ማምጣት ባለመቻሉ የእርቅ መንገድን መጠቀም አለበት የሚለው ይገኝበታል።

አቶ ሻፊ ግን መንግሥት ለዚህ በሩ ክፍት ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ “ታጣቂው እንዲሁ ለቃል ካልሆነ በቀር ለሰላም ዝግጁ አይደሉም” ሲሉ ይከሳሉ።

የፖለቲካ ፍላጎት

የኦሮሚያ ክልል በአገሪቱ ካሉት ክልሎች በቆዳ ሰፋቱም ሆነ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚው ነው። በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች የክልሉ መንግሥት የአገሪቱን ፖለቲካ መቆጣጠር የሚፈልጉ አካላት ክልሉን ዒላማ ሊያደርጉት ይችላሉ የሚል ስጋት አለው።

አቶ ሻፊም ይህን ሁኔታ “የፖለቲካ ፍላጎት ነው” ሲሉ ይገልጹታል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ፍላጎታቸው ምንም ቢሆን ግባቸው ግን ተመሳሳይ መሆኑን ያስረዳሉ። “አገር ማፍረስ፣ ሕዝብ ማፈናቀል፣ ንብረት ማውደም፣ ሁከት መፍጠር፣ ከተቻለም ይህን መንግሥት አፍርሰው የሽግግር መንግሥት መመስረት ነው” በማለት ይናገራሉ።

ከዚህ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትን በይፋ ሲኮንኑ አይስተዋልም። በዚህም ታጣቂዎች የልብ ልብ እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗቸዋል ይላሉ።

ሌሎች ምክንያቶች

ለዓመታት የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በየአካባቢው የሚስተዋሉ ብሔር ተኮር ግጭቶች ተበራክተዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚታየውም ከዚህ የሚለይ አይደለም።

ለበርካታ ዓመታት በሰላም አብረው ይኖሩ የነበሩ ማኅበረሰቦች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን አዲስ ነገር እንዳጋጠማቸው ይናገራሉ።

ሰዎች እርስ በእርሳቸው እንዲጠራጠሩ እና በሕዝቦች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት እንዲሻክር የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የማኅበረሰብ አንቂዎች አሉታዊ ሚና እንደተጫወቱ በርካቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሦስት አስርት ዓመታት በበላይነት ሲመራ የቆየው ህወሓት በሕዝቦች መካከል መጠራጠርና ግጭት በመፍጠር በመሆኑ አሁን የሚታየው ሁኔታም የዚያ ተከታይ እንደሆነ ባለሥልጣናት ይናገራሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ሰፊውን የአገሪቱን ሕዝብ ቁጥር በሚሸፍኑት ወጣቶች ዘንድ የተንሰራፋው ሥራ አጥነት እና የእርሻ መሬት እጥረትን የመሳሳሉ ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ለሰላም እጦት እንደ ምክንያት ይቀርባሉ።

* በዚህ ታሪክ ውስጥ የተካተቱት ሰዎች ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀዋል