ባልደራስ ከአሜሪካ ኢምባሲ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያየ

በቅርቡ ከግፍ እስር የተፈቱት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ከፍተኛ አመራርና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባሉ አቶ ስንታየሁ ቸኮል አዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ የሥራ ሓላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮችና በፓርቲው እንቅስቃሴ ዙሪያ ተወያይተዋል። አቶ ስንታየሁ ከኢምባሲው የፖለቲካና ምጣኔ ሃብት ጉዳዮች አማካሪ ጆን ጂ. ሮቢንሰን እና ከምክትል የፖለቲካዊ ምጣኔ ሃብት ጉዳዮች አማካሪው ኦስማን ታት ጋር በነበራው ውይይት ስለ አማራ ፋኖ ወቅታዊ እንቅስቃሴ አንስተዋል። ፋኖ የኢትዮጵያ አንድነት መሰረት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ስንታየሁ መንግሥት የሚያደርግበት ትንኮሳ ተገቢ አለመሆኑንም ተናግረዋል።
ሕወሓት የከፈተው ጦርነት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የሚፈታተን መሆኑንም አስረድተዋል። በመሆኑም ፓርቲያቸው ‘ሕወሓት በማዕከላዊ መንግሥቱ የጥምር ጦር መመታትና ለኢትዮጵያ ህልውና ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ መድረስ አለበት’ ብሎ እንደሚያምን አብራርተዋል።
በውይይቱ በወለጋ በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጅምላ ጭፍጨፋ፣ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ፣ የሰንደቅ ዓላማና የሕገ መንግሥቱ ብሎም የባልደራስ አመራሮች የእስር ቤት ቆይታዎች ተነስተዋል።
ከአመታት በፊት የጀመረው የአማሮች ጅምላ ጭፍጨፋ አሁንም በወለጋ እንደቀጠለ መሆኑን የገለፁት አቶ ስንታየሁ ቸኮል ከጭፍጨፋ የተረፉ አማሮች ዛሬም የድረሱልኝ ጥሪ እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሕገ መንግሥቱም የሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንጂ የሕዝብ ተሳትፎ የሌለበት በመሆኑ በሕዝብ ተሳትፎ እንዲሻሻል ባልደራስ እየታገለ መሆኑን አስረድተዋል። ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል የሰንደቅ አላማ ጉዳይም አብሮ መልስ እንደሚያገኝም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሀገራዊ የምክክር መድረክ መከፈቱን ድርጅታቸው በበጎ እንደሚረዳው ገልፀው አፈፃፀሙ ላይ ግን ተቃውሞዎች እንዳሏቸው ጠቁመዋል። በተለይም ኮሚሽኑ በገለልተኛ አካላት መቋቋም ሲገባው በመንግሥታዊው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት መቋቋሙ ጥርጣሬን አጭሮባቸዋል። መንግሥት ተዓማኒ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል። ሆኖም በአገራዊ ምክክሩ ፓርቲያቸው ስለመሳተፍ አለመሳተፉ የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወደ ፊት የሚወስነው መሆኑን ተናግረዋል።