በሳኡዲ አረቢያ መፍትኄ አልባው የኢትዮጵያውያን መከራ በሚቀጥለው ሳምንት አንድ መፍትሄ ይኖረዋል ተባለ ።

DW : ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ዓረቢያ የተለያዩ እስር ቤቶች ለበርካታ ወራት ያለምንም ጠያቂ እየማቀቁ መኾናቸውን ለዶይቸ ቬለ ተናገሩ። ኢትዮጵያውያኑ ከሰባት ወራት በላይ እስር ቤት በቆዩባቸው ጊዜያት ውስጥም ከመንግሥት አካልም ኾነ ከሌላ የሚመለከተው አካል የጠየቃቸው እንደሌለ ገልጠዋል። በጉዳዩ ላይ ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ጋር ለመነጋገር በገንዘብ ሚኒስትር አሕመዴ ሽዴ የሚመራ የልዑክ ቡድን ትናንት ሳዑዲ ዓረቢያ መግባቱን ሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትናንት ዐስታውቋል። ምናልባትም በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ አለያም ረቡዕ ስለ እስረኞቹ አዲስ ነገር ሊኖር እንደሚችልም ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ በበርካታ ሺህዎች የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን ሳዑዲ ዓረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ እጅግ በአሰቃቂ ኹኔታ እየማቀቁ እንደሆነ ተገለጠ። ሳዑዲ ዓረቢያ ጂዳ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት አቶ መሐመድ ሲራጅ ዑመር የባለቤታቸው ወንድም በእስር ቤት ውስጥ ያየው እጅግ የሚያሰቅቅ እንደነበር ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
«በአጋጣሚ የባለቤቴ ወንድም እስር ቤት ነበር እና አሞት ለሕክምና ሲኼድ ምነው እኔ ይህን ሕክምና ከማገኝ ባላይ ቀርቶብን ነው ያለው። እዚያ ሕክምና ቦታ ላይ ያሉትን ሲያይ ማለት ነው። በጣም ዘግናኝ ነው። ዐይኖቻቸው በህክምና እጦት የማያዩ፤ እግራቸው የተቆረጡ፤ ብቻ የተለያዩ መናገር የሚከብዱ በጣም ብዙ ችግሮች አሉ።»
ይህ ብቻ ሳይሆን የአጎታቸውም ልጅ በወለደች በሳምንቷ ለእስር መዳረጓን አቶ ሲራጅ ገልጠዋል። በአጠቃላይ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ነዋሪ ከኾኑ ኢትዮጵያውያን መካከል እስሩ ቤቱን ያላንኳኳ የለም ሲሉም አክለዋል።

«በጣም ብዙ ሰው ነው ያለው። ይኼን ያህል ማለት ይከብዳል። ምክንያቱም በእየ ሁሉም አምበር [የእስር ክፍል]የተለያየ ቦታ ነው ያለው። እሱ ያለበት አምበር አለ፤ በሴቶችም እንደዚሁ የአጎቴ ልጅ በወለደች በሳምንቷ የገባች አለች። ሌሎችም እንደዚሁ በዐርባ ቀናቸው የገቡ እስካሁን ድረስ እስር ቤት ያሉ አሉ። በሁሉም በኩል ያለው እክግ በጣም የሚዘገንን እና ከባድ ነገር ነው። እንደቀላል የኾነ ምን ልበልህ ሁሉ ነገር የተሟላላቸው አይደሉም። በምግብ ደረጃ ራሱ የተሟላ ነገር የሚያገኙ አይደለም፤ ከእዚህ እባካችሁ ብር ላኩ እያሉ ብር እንልካለን። ብስኩት ገዝተው የተወሰነ ነገር ራሳቸውን ለማጽናናት የሚያደርጉበት ነገር አለ። የሰውም ብዛት በጣም ብዙ ነው። ብቻ በጣም ከባድ እና ፈታኝ ሕይወት ውስጥ ነው እየኖሩ ያሉት።»
50 እና 60 እየተባለ ቁጥር በሚሰጣቸው እንደሳቸው አባባል አምበሮች ወይንም የእስር ክፍሎች ከእዚህ ቀደም ይገቡ የነበሩት በባሕር እና በበረሃ ጉዞ በአንጻሩ መከራን የተቋቋሙ ነበሩ ብለዋል። የአሁኖቹ ግን በአብዛኛው የተደላደለ ኑሮ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ይገፉ የነበሩ ናቸውም ሲሉ አክለዋል። አቶ መሐመድ አብዛኞቹ ሥራና የመኖሪያ ፍቃድ የነበራቸው፤ በአንዳንድ ምክንያቶች ለእስር የተዳረጉ ናቸውም ብለዋል።

አብዛኞቹ እስረኞች በዋናነት ሪያድ እና ጅዳ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ እንደ ጂዛን እና አካባቢው ባሉ እስር ቤቶችም ኢትዮጵያውያኑ እየማቀቁ ነው። ከ7 ወራት በፊት 40 ሺህ ኢትዮጵያውያን በተከታታይ በረራዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ከተደረገ በኋላም ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ኢትዮጵያውያኑን እያደኑ ማሰሩ አሁንም መቀጠሉን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የሦስት ልጆች አባት የኾኑት አቶ ሐምዛ ሙሐመድ ካለፉት ሰባት ወራት አንስቶ በሹመይቴ እስር ቤት፤ አምበር 52፤ ኮድ ቁጥር A ውስጥ እየማቀቁ ይገኛሉ። አብረዋቸው ከ200 በላይ እስረኞች እንደሚገኙ፤ ሰሞኑን እስር ቤት ውስጥ ወረርሺኝ ገብቶ እንደነበርም ለዶይቸ ቬለ ተናግሯል።

Saudi Arabien I Äthiopische Migranten werden in ihr Herkunftsland zurückgebracht «ያው እንግዲህ እዚህ የተወሰኑ ስቃዮች አሉ። ብርድ ልብስ ራሱ ችግር አለ። እና ሲሚንቶ ላይ የሚተኛ ሰው አለ። በተጨማሪም በሽታ ያመናል። በተለይ እንደ ወረርሽኝ ነገር በብዛት እየገባ ብዙ ጊዜ ነው፤ ሰሞኑን ራሱ ታመን ነበር። እንደገና ያው የተለያዩ ነገሮች አሉ። እንግዲህ አላህ መፍትኄውን ያምጣልን ነው የምንለው።»

አቶ ሐምዛ ሙሐመድ ሳዑዲ ዓረቢያ በመኖሪያ ፈቃድ ላለፉት ዐሥር ዓመታት እንደኖሩ ይናገራሉ። ትዳር መስርተው ሦስት ልጆች ያፈሩ ሲሆን፤ ልጆቻቸው አሁን ወደ ኢትዮጵያ ተልከዋል። ባለቤታቸው ግን እንደሳቸው እስር ቤት ይገኛሉ። ለእስር የተዳረጉት የመኖሪያ ፈቃዳቸውን የሚያድስላቸው ጠፍቶ ጊዜው በማለፉ ነው። ከታሰሩበት ጊዜ አንስቶ የጠየቀን አካል የለም ሲሉም ተናግረዋል።

«ይኸው ሰባት ወራችን ነው አንድ ቀን ኤምባሲ እንኳን መጥቶ ምንድን ነው ችግራችሁ? ብርድ ልብስ የሚያጡ ልጆች አሉ። ሕክምና የሚያስፈልጋቸው፤ በመሣሪያ የተመቱ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ልጆች አሉ። ሌላው ቀርቶ ዐይናችን እያሳከከ ዐይናቸው የሚጠፋ ልጆች አሉ በዚያ የተነሳ።  ይኼ ሰውነታቸው ላይ የቆሳሰለ ምናምን ሕክምና የሚያስፈልግ፤ እና እስካሁን ድረስ መጥቶ የጠየቀን አንድም አካል የለም። ያው እኛ ተስፋችን ምናልባት መንግሥት ልዑካን ቡድን ልኳል የሚባል ነገር አለ፤ እንግዲህ በቅርብ ጊዜ ወደ ሀገራችሁን ያስገቡን ብለን ተስፋችን እሱ ነው። ከዚያ ውጪ እስካሁን ድረስ። በስቃይ ላይ ነው ያለነው። ምንም ይኼ ነው የሚል የመንግሥትም አካል ያየንም የለም። ከእኛም ከኢትዮጵያዊ ይኼ ነው ብሎ መጥቶ የጠየቀን ሰው የለም እስካሁን ድረስ።»

ስለ ኢትጵያውያኑ ጉዳይ ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ለመነጋገር በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የሚመራ የልዑክ ቡድን ትናንት ሳዑዲ ዓረቢያ መግባቱን ሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዐስታውቋል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ አምባሳደሮች ጋር ብንደውልም የአንደኛው የእጅ ስልክ በተደጋጋሚ ቢጠራም አይነሳም፤ ሌላኛው እስከ ማክሰኞ አለያም ረቡዕ እንድንጠብቅ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያኑን በተደጋጋሚ ከእስር አስፈትቶ ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ሥራ ቢሠራም፤ ችግሩን በዘለቄታው መፍታት ግን እስካሁን አልተቻለም።