ምንዛሪ፣ ጥሬ ገንዘብ፣ ገንዘብ እና የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ ( ጌታቸው አስፋው )

የአንድ አገር ኢኮኖሚ በሁለት ዋና ዋና ዘርፎች ይከፈላል፤ የምርት ኢኮኖሚ ዘርፍ እና የምርት ኢኮኖሚውን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማገበያየት የሚረዳ የገንዘብ ኢኮኖሚ ዘርፍ በሚል። ሁለቱ እንዲደጋገፉ በተለይም የገንዘብ ኢኮኖሚው የምርት ኢኮኖሚውን እድገት እንዳያደናቅፍ በጥናትና በዕቅድ መመራት አለባቸው፡፡ የገንዘብ ኢኮኖሚው ዘርፍ በጥናትና በዕቅድ ካልተመራ በቀር ኢኮኖሚውን ቢያሳድግም የሰዎችን የኑሮ ደረጃ አራርቆ አንዱ በድህነት እንዲማቅቅ እና ሌላው በሀብት እንዲምነሸነሽ የማድረግ አቅም ስለአለው፡፡

የገንዘብ ኢኮኖሚውን በጥናትና በዕቅድ ለመምራት ሦስቱን በጥሬነት ደረጃ የሚለያዩ የገንዘብ ዓይነቶች ምንዛሪን፣ ጥሬ ገንዘብን፣ ገንዘብን፣ ትርጉማቸውን ለየብቻ ማወቅ ያስፈልጋልለ፡፡ ሦስቱን በአላስፈላጊ ቦታ ጠቅሎ በአንድ መጠሪያ ስም ገንዘብ ብሎ መጥራት ወይም አቀላቅሎ መናገር ትክክል አይደለም፡፡ በግሎባላይዜሽን ዓለም ውስጥ ከዓለም ሕዝብ ጋር ተመሳሳይ የምንዛሪ የጥሬ ገንዘብና የገንዘብ ቋንቋ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ምንዛሪን- Currency ጥሬ ገንዘብን- Money ገንዘብን- Finance ብለው ነው የሚጠሩት፡፡

በኢትዮጵያ ግን እስከአሁን ድረስ የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሙያዎችና ባለሥልጣናት፣ የብሔራዊ ባንክ ባለሙያዎችና ባለሥልጣናት የንግድ ባንኮች ባለሙያዎችና ባለሥልጣናት ሌሎች ከምንዛሪ ከጥሬ ገንዘብና ከገንዘብ ጋር በተያያዘ አገልግሎት የሚሰጡ የመንግስትና የግል ድርጅቶች ባለሙያዎችና ባለሥልጣናት ሳይቀሩ በንግግሮቻቸውም ሆነ በጽሑፎቻቸው ምንዛሪን ጥሬ ገንዘብን እና ገንዘብን በአንድ መጠሪያ ስም ገንዘብ ብለው ስለሚጠሩ በቋንቋቸው ለሶስቱ የተለያዩ ፖሊሲዎች መቅረጽ ይቸገራሉ፡፡

የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በጥሬ ገንዘብ ብዛት ነው፤ በውጭ ምንዛሪ መጣኝ የአገር ውስጥ ምንዛሪ ዋጋ የሚረክሰውም በጥሬ ገንዘብ ብዛት ነው፤ የሥራ አጥነት የሚፈጠረው ግን በጥሬ ገንዘብ ማነስ ወይም በገቢ ማነስ ነው፡፡ የጥሬ ገንዘብ መብዛት የጥሬ ገንዘብ ማነስ ምን ዓይነት እንቆቅልሽ ነው?

የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መብዛትና ማነስ ለኢኮኖሚው ያለውን እንድምታ አክርረው የተከራከሩ ሁለት ታዋቂ ኢኮኖሚስቶች የማክሮ-ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጠንሳሽ ነው በመባል የሚታወቀውና ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ድርጅትንና የዓለም ባንክን ጠንስሶ ያቋቋመው ኢኮኖሚስት ኬንስና ተከታዮቹ በአንድ ወገን እና በሌላ ወገን የእነርሱ አመለካከት ተቃራኒ የሆኑት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሪቻርድ ኒክሰንና ሮናልድ ሬጋን አማካሪ በነበረው በኢኮኖሚስት ሚልተን ፍሬድማን የሚመሩ የጥሬ ገንዘብ ኢኮኖሚስቶች ናቸው፡፡

ኬንስና ተከታዮቹ ቢያንስ በአጭር ጊዜ ውስጥ የጥሬገንዘብ አቅርቦት መጨመር የወለድ መጣኝ እንዲቀንስ በማድረግ መዋዕለንዋይን፣ ገቢን፣ ምርትን፣ ሥራቅጥርን፣ ያሳድጋል ኢኮኖሚው እንዲስፋፋም ያግዛል የሚል አመለካከት ሲይዙ ፍሬድማን እና ተከታዮቹ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጨመር ውጤት የሚጎላው ኢኮኖሚውን በማሳደግ ላይ ሳይሆን በዋጋ ንረት እና በውጭ ምንዛሪ መጣኝ መውደቅ ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ላይ ነው የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ በተከታታይ ለረጅም ጊዜ የቆየ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጨመር መዋዕለንዋይን ከማሳደግና ኢኮኖሚውን ከማስፋፋት ይልቅ የዋጋ ንረትና የውጭ ምንዛሪ መጣኝን በመሳሰሉ ገንዘብ ነክ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ውጤት እንደሚያመጡ ግን ሁለቱም ወገኖች ይስማማሉ፡፡

ጥሬ ገንዘብ ዋናው የምርት ኢኮኖሚው ዘዋሪ ነው የሚለው ሚልተን ፍሬድማን የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት በሰው ፍላጎት በዘፈቀደ ከሚወሰን በሕግ በተደነገገ በዓመት ከሦስት እስከ አምስት በመቶ ባልበለጠ ዕድገት እንዲገደብ ይመክራል፡፡ ኬንስ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት በአጭር ጊዜ ውስጥ የወለድ መጣኝን በመቀነስ መዋዕለንዋይን ገቢን ምርትን ሥራ ቅጥርን እና ኢኮኖሚውን ያሳድጋል ቢልም ከጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ ይልቅ በዋናነት ለኢኮኖሚ እድገት የሚያስፈልገው የመንግሥት ከባንክ በመበደር ከገቢው በላይ ወጪ ማድረግ የበጀት ጉድለት ፖሊሲ (Deficit Financing) እንደሆነ ይመክራል፡፡

እነኚህ ሁለት የጥሬገንዘብና የመንግስት በጀት ጉድለት የኢኮኖሚ ዕድገት አመለካከቶች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመተንተን የሚያስችሉ ጽንሰ-ሐሳቦች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት ከገንዘብ ሚንስቴር ከሚገኘው የመንግሥት በጀት ጉድለት መረጃ በተጨማሪ በብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት ጥሬገንዘብ ከልክ በላይ በሆነ መጠን በአማካይ ከሃያ አምስት በመቶ በላይ ስላደገ በአንድ በኩል ኢኮኖሚውም ሰፍቷል በሌላ በኩልም የዋጋ ንረትና የውጭ ምንዛሪ መጣኝም ሕዝቡንና አምራቹን ለምሬት ዳርገዋል፡፡

ሆኖም ግን በኢትዮጵያ በጥሬ ገንዘብ ከልክ በላይ መጨመር ምክንያት የግል መዋዕለንዋይ አላደገም መዋዕለንዋይን በሚያሳድገው በፈጠራ ሥራ ምትክ የተገላቢጦሹ የሥራ ፈጠራ ስለተሰበከ የፍጆታ ምርት በመበረታታት ለወንደላጤውና ለሴተላጤዋ ምግብ ቀቅሎ፣ ለባለሥልጣኑ ሰብቆ፣ በጉልበቱ መግዛት ለሚፈልገው ጠመንጃ ተሸክሞ፣ ለወስላታው ደልሎ፣ ለጨፋሪው ዘፍኖ፣ ለወሬ ሱሰኛው የባጥ የቆጡን ወሬ አውርቶ፣ በአገልግሎት የሰውን ርካሽና ጋጥ ወጥ ሱስ አርክቶ፣ ጥሬ ገንዘብ ለማግኘት መጣጣር ተመራጩ መንገድ ሆነ፡፡

እንደነዚህ ዓይነት የፍጆታ ምርቶች ዕድገት ኑሮ በልማዳዊ መንገድ ተስፋፍቶ ማህበራዊ ቀውስ እስከሚያስከትል ድረስ አብጦ እንዲቀጥል ያደርጋሉ እንጂ የመዋቅር ሽግግር (Structural Transformation) አያመጡም፡፡

ኢትዮጵያ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ነው ያለችው በበጀት ጉድለት ተወጥራለች፣ ለሜጋ ፕሮጀክቶች የተበደረችውን መክፈያ ጊዜ ደርሶ ተጨንቃለች የዋጋ ንረትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ቀስፈው ይዘዋታል፤ የገቢ ሥርጭቱ አለመመጣጠን ሕዝቡን እያመሰው ነው፡፡ ለእነኚህ ሁሉ ችግሮች መፍትሔ ከገንዘብ ኢኮኖሚው ሥርዓት ስታፈላልግ ግን አትታይም፡፡

ኢኮኖሚ የሚለካው በገንዘብ ነው ኢኮኖሚን በገንዘብ ለመለካት መጀመሪያ ገንዘብን ራሱን መለካት ያስፈልጋል፡፡ ገንዘብን ለመለካትም መጀመሪያ በጥሬነት ደረጃ ልዩ ልዩ ትርጉሞቹን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የምንዛሪን፣ የጥሬ ገንዘብን፣ የገንዘብን፣ ትርጉም በጥሬነታቸው ደረጃ ለያይቶ ያላወቀ ምንዛሪንም ጥሬ ገንዘብንም ገንዘብንም ኢኮኖሚውንም መለካት አይችልም፡፡

በቴሌቪዥን መስኮቶች እንደምንመለከተው በተፈጥሮ ቁጥሮች መለኪያ ከመነጋገር አልፎ በአቅጣጫ አመልካች መለኪያ (Index) በቅጽበት ለክቶ ከመቶ ፐርሰንት ወደ ላይ የወጣውን እና ወደ ታች የወረደውን አይቶ ተርጉሞ በገንዘብ ቋንቋ መነጋገር ከጀመረ በገንዘብ ቋንቋ መገበያየት ከጀመረ ከዓለም ሕዝብ ጋር የምንዛሪን የጥሬገንዘብን የገንዘብን ትርጉም የማያውቅ ሰው ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ቋንቋ ሊነጋገር አይችልም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሸቀጥን የሚያገበያይ በርካታ ምንዛሪና ጥሬገንዘብ ገበያ ውስጥ እየተዘዋወረ የዋጋ ንረትን እየፈጠረ ለካፒታል የሚሆን ገንዘብ እጥረት እንዳለ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ምንዛሪን ጥሬገንዘብን እና ገንዘብን ግን ብዙዎች በንግግሮቻቸውና በጽሑፎቻቸው በጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level) ለያይተው ተናግረው አያውቁም፡፡

ለመሆኑ በገንዘብ ኢኮኖሚ ውስጥ ጥሬነት ማለት ምን ማለት ነው? ስንትና ምን ዓይነት የጥሬነት ደረጃዎችስ አሉ? የገንዘብ ገበያ ከጥሬነት ጋር እንዴት ይዛመዳል? በኢትዮጵያ የጥሬ ገንዘብ ትርጉም መሠረት አንደኛው ብሔራዊ ባንክ የሚያሰራጨው ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ (Currency) ሲሆን፣ ሁለተኛው ንግድ ባንኮች ምንዛሪውን አርብተው የሚፈጥሩት የብድር ጥሬ ገንዘብ (Credit Money) ናቸው፡፡ ለመሆኑ እያንዳንዳቸው ለኢኮኖሚው ምን ያህል ጥሬ ገንዘብ ይፈጥራሉ፡፡ ከሁለቱ በዋናነት የዋጋ ንረት የሚፈጥረውስ የትኛው ነው፡፡

ወለድ ከጥሬነት ለመለያየት የሚከፈል ዋጋ ነው ከጥሬነት መለየት ማለትም ከምንዛሪ ከጥሬ ገንዘብ ከገንዘብ ተለይቶ መቆየት ማለት ነው፡፡ ከጥሬነት ተለይቶ ለመቆየት የሚከፈለው ዋጋ ወለድም በጥሬነት ደረጃ ይለያያል፡፡ ቁጠባና መዋዕለንዋይም በወለድ መጣኝ ላይ የተመሠረቱ ሆነው በተራቸውም የምርት ኢኮኖሚው ዕድገት የተመሠረተባቸው የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ነዳጅና ሞተር ናቸው፡፡ እነኚህን ግንኙነቶች በውል ካላወቁ የምርት ኢኮኖሚውን ዕድገት ማቀድም አይቻልም፡፡

ንግድ ባንኮች የዋጋ ንረት አስራአምስት በመቶ በሆነበት አገር ውስጥ ለቆጣቢው ድሃ ገበሬና ድሃ ወዛደር ሰባት በመቶ ወለድ ብቻ እየከፈሉ በየዓመቱ በቁጠባ ተቀማጩ በስምንት በመቶ ማክሰራቸው አልበቃ ብሎ ብሔራዊ ባንክ አትሞ የሚያሰራጨውን አንድ አራተኛ የአገር ውስጥ ምንዛሪ (Currrency) ጥሬ ገንዘብ አርብተው ለሀብታሞች በሚሰጡት ሦስት አራተኛ የአገር ውስጥ ብድር ጥሬ ገንዘብ (Credit Money) የዋጋ ንረት መንስኤ ሆነውም ድሃውን ለስቃይ ዳርገዋል፡፡

በሌላ በኩል የድሃውን ተቀማጭ ከባንክ ተበድረው መዋዕለንዋይ የሚያፈሱ ሀብታሞች በዐሥራ አምስት በመቶ ወለድ እንኳ፣ ቢበደሩ በዓመቱ መጨረሻ ብድራቸውን ሲመልሱ በዋጋ ንረት ምክንያት የመግዛት አቅሙ በዐሥራ አምስት በመቶ የቀነሰ ብድር ለባንኩ ስለሚመልሱ፣ ወለዱና የዋጋ ንረቱ ተጣጥተው በባዶ ወለድ እንደ ተበደሩ ይቆጠራል፡፡

በ1980ዎቹ መጀመሪያ ቁጥሩ ከዐሥር በታች የነበረ ነጠላ አሃዝ ቢልዮን ብር ገደማ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን ከመቶ እጥፍ በላይ አድጎ ዛሬ ወደ ትሪልየን እየተጠጋ ነው፡፡ ማን ነው የጥሬ ገንዘቡን መጠን እንደዚህ የሚያሳድገው? ለምንስ ነው የሚያሳድገው? ሸቀጥን ለማገበያየት ብቻ የሚበቃ ትክክለኛውን ተፈላጊ የጥሬ ገንዘብ መጠንስ እንዴት ያውቃል?

በብዙ አገራት ውስጥ ብሔራዊ ባንኮች ከመንግስት ተጽዕኖ ነፃ ሆነው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠንን ሲወስኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የመንግሥት አገልጋዮች በመሆናቸው አድርጉ ያላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ በኢትዮጵያ ከልክ ያለፈ ጥሬ ገንዘብ ገበያ ውስጥ ተሰራጭቶ የዋጋ ንረትን እንደፈጠረ ስንቶቻችን እናውቀለን? ብሔራዊ ባንኩ እንደ ቀድሞ ጊዜ የወርቅ መጠባበቂያ ዋስትና የሌለውን በህዝብ እምነት ብቻ ተማምኖ የሚያትመውን ምንዛሪ እንደፈለገው እሰራጭቶ ኑሯችንን ምድራዊ ሲዖል እንዳላደረገብን ምን ያህል እንተማመናለን፡፡

ንግድ ባንኮች በቁጠባ መልክ የተቀመጡትን ምንዛሪዎች አርብተው በሚሰጡት ብድር የሸቀጦች ዋጋ እንዳይንር ብሔራዊ ባንኩ ተቆጣጥሯቸዋል ብለንስ ምን ያህል ልናምን እንችላለን፡፡ ብሔራዊ ባንኩ ምንዛሪ በማሰራጨት ተግባሩና ንግድ ባንኮችን በመቆጣጠር ሥራው ምን ያህል ከሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ተጽዕኖ ነፃ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ መጣኝ የብራችን ዋጋ እንዳይረክስ ምን ያህል ከጥሬገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲው ጋር አቀናጅቶ በፖሊሲ መርቷል፡፡

እርግጠኛ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ (Effective Real Exchange Rate) የእኛ የአገር ውስጥ ምንዛሪ ብር በአገር ውስጥ የሸቀጦች ገበያ የመግዛት አቅም ከሌሎች በኢምፖርት- ኤክስፖርት ንግድ ከተጣመሩ አገራት የውጭ ምንዛሪ በአገሩ የሸቀጦች ገበያ ከመግዛት አቅም ጋር ተመዝኖና ተነጻጽሮ የሚያገኘው አማካይ ዋጋ ነው፡፡

ይህ እርግጠኛ የምንዛሪ መጣኝ መለኪያ በምንዛሪ ገበያ በብር ፍላጎትና አቅርቦት ከሌላ አገር ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት ጋር ተነጻጽሮ ከሚለካው ምስለ የምንዛሪ መጣኝ (Nominal Exchange Rate) የሚለየው በሸቀጦች የዋጋ ንረት በሚከሰት የምንዛሪው የመግዛት አቅም መዳከም ምክንያት የመመነዛዘሪያ መጣኙ መውደቁን ስለሚገልጽ ነው፡፡ በአጭር አነጋገር የምንዛሪ መጣኝ የሚለካው በውጭ ምንዛሪ ወይም በገንዘብ ገበያ መስተጋብር ብቻ ሳይሆን በሸቀጥ ገበያ መስተጋብርም ነው፡፡

አገራት የአገራቸውን በኤክስፖርት ተወዳዳሪነት ለመለካትም የሚጠቀሙት ሸቀጦችን በመግዛት አቅሙ ተመዝኖ የተለካውን እርግጠኛውን የውጭ ምንዛሪ መጣኝ በማስላት ነው፡፡ በ2010 የጥቅምቱን የብር ምንዛሪ መጣኝ ለውጥም ሃያ ሁለት ብር ብቻ የነበረውን ምስለ የብር ምንዛሪ መጣኝ ሃያ ሰባት ብር እንደደረሰ ከተገመተው ከእርግጠኛው የብር ምንዛሪ መጣኝ ጋር ለማቀራረብ የተወሰደ እርምጃ ነው ልንል እንችላለን፡፡

ብሔራዊ ባንኩ በራሱ የበርካታ ዓመታት የፖሊሲ ድክመቱ በዋጋ ንረት አማካኝነት የፈጠረውን የእርግጠኛ ምንዛሪ መጣኝ እና የምስለ ምንዛሪ መጣኝ ልዩነት ቀዳዳ መድፈኑ ነው፡፡ ቀዳዳ ስንፈጥር ቀዳዳ ስንደፍን ዘመን አልፎ ዘመን ይተካል ዘንድሮም ያው ለከርሞም ያው ነው፡፡

በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ከሌላው አገር የዋጋ ንረት በበለጠ ቁጥር የብር ሸቀጦችን የመግዛት አቅም ስለሚቀንስ የብር እርግጠኛ ምንዛሪ መጣኝ ይወድቃል፡፡ በየዓመቱ የዋጋ ንረቱ ልዩነት እየቀጠለ በመጣ ቁጥር የብሩ እርግጠኛ ዋጋ እየተዳከመ በብርና በሌላው አገር የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት የገበያ ዋጋ መሠረት ከተለካው ምስለ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ ጋር ሳይመጣጠን ይቀራል፡፡ ይህም በጥቅምት 2010 እንደተደረገው በምንዛሪዎቹ ፍላጎትና አቅርቦት በገንዘብ ገበያ መስተጋብር የተለካው ምስለ መመነዛዘሪያ መጣኝ በሸቀጦች ገበያ መስተጋብር ከሚለካው እርግጠኛው የውጭ ምንዛሪ መጣኝ ጋር እንዲስተካከል እንዲከለስ ያስገድዳል፡፡ ይህ እንዳይሆን ከውጭ ምንዛሪ መጣኝ አለካክ ሥርዓት ጋር የተገናዘበ የዋጋ ንረትን የማያስከትል የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲ መቅረጽ የመንግስት ወይም የብሔራዊ ባንኩ ግዴታ ነበር፡፡ የጥቅምቱ 2010 የብር ዋጋ መርከስ በኢምፖርትና ኤክስፖርት ሸቀጦች ዋጋ ላይ ውጤት ይኑረው እንጂ የመርከሱ ምክንያት ሰው ስለፈለገው ብቻ የሆነ ሳይሆን በራሱ ምክንያት የሆነ ነገር ነው፡፡ ኤክስፖርተሮች ከምንዛሪ መጣኙ ለውጥ በሚያገኙት ጥቅም ይደፋፈራሉ የተባለው ግን ላይ ላዩን ለሚመለከት ሰው ብቻ የሚመስል ነገር ነው፡፡ ኤክስፖርተሮች ከምንዛሪ ለውጡ በኋላ በሚፈጠረው የኤክስፖርት ምርቶች በአገር ውስጥ ሸመታ ተጠቂም ናቸው፡፡

በአንድ ወቅት የቡና ኤክስፖርተሮች በብር ተመንዝሮ አንድ መቶ ሠላሳ ብር ለሚደርሳቸው ዋጋ የውጭ ምንዛሪውን ለኢምፖርት ሸቀጥ ለመጠቀም ብለው ከአገር ውስጥ ቡናውን በአንድ መቶ ሀምሳ ብር ገዝተው ከስረውም ይሸጡ እንደነበር በምንዛሪ ለውጡ ምክንያት የሚመጣባቸውን በአገር ውስጥ የቡና ዋጋ መጨመርም መቋቋም እንደሚኖርባቸው የሚያመለክት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሸቀጦች ዋጋ ንረት ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎች ከኢትዮጵያ ጋር ተነጋጋጅ አገራት ሸቀጦች ዋጋ ንረት የበለጠ ሲሆን በምንዛሪዎቹ ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ተመርኩዞ የተወሰነው ምስለ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ ግን ሸቀጦችን በመግዛት አቅም ላይ ተመርኩዞ የሚወሰነውን እርግጠኛውን መመነዛዘሪያ መጣኝ አላንጸባረቀም፡፡

በጥቅምት ወር የተደረገው የምንዛሪ መጣኝ ለውጡ ስለዚህም የሚያመለክተው የዋጋ ንረት ለምንዛሪ መጣኝ ለውጥ ምክንያትም ውጤትም ሊሆን እንደሚችል እና የምንዛሪ መጣኝ ለውጥም ለዋጋ ንረት ምክንያትም ውጤትም ሊሆን መቻሉን ነው፡፡ በጥቅምት የብር ዋጋ ከረከሰ በኋላም የሸቀጦች ዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ ጨመሮ እስከ ዐሥራ አምስትና ሃያ በመቶ ደርሷል፡፡

በኢምፖርት-ኤክስፖርት የውጭ ንግድ ሸሪኮቻችን አገሮች ውስጥ ግን የዋጋ ንረት ከሁለትና ሦስት በመቶ አይበልጥም፡፡ ስለዚህም መቼ እንደሆነ ባይታወቅም የሌላ ዙር የብርን ዋጋ ማርከስ እርምጃ መጠበቅ አለብን፡፡ የዋጋ ንረትና የብር ዋጋ መውደቅ እየተደጋገፉ በየተራ በመቀጠል ከዘመን ወደ ዘመን ያሸጋግሩናል፡፡

ኢትዮጵያ ስለገንዘብ ኢኮኖሚ ገና ያልተጠናባት ኢኮኖሚዋ ግን በ“ሾላ በድፍን” ተለክቶ ይህን ያክላል ተብሎ የሚነገርባት አገር ናት፡፡ የምርት ኢኮኖሚውን ለመምራት መለካት ያስፈልጋል፡፡ ለመለካትም የገንዘብ ኢኮኖሚውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አዲሱ ኢሕአዴግ የአሮጌውን ኢሕአዴግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳለ ማስቀጠል ስለሚሻ፣ በፖለቲካው መደማመርን ቢያሳካም በኢኮኖሚው በዝባዥና ተበዝባዥን ማደማመር ይሳነዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሮናልድ ሬጋን ስለዋጋ ንረት ሲናገሩ፡- “የዋጋ ንረት እንደ አዞ ኃያል፣ እንደ የታጠቀ ዘራፊ አስፈሪ፣ እንደ አልሞ ተኳሽ ገዳይ ነው፤” ብለው ነበር፡፡ መንግሥት ከመጠን በላይ ምንዛሪ አትሞ የሸቀጦችን ዋጋ በማስወደድ ከሕዝብ በነፃ የሚወስደው ሀብት የዋጋ ንረት ግብር (Inflationary Taxing) ይባላል፣ የሶቭየት ኅብረት ሶሻሊስት መንግሥት መስራች ሌኒንም ስለዚህ ጉዳይ የሚከተለውን ተናግሮ ነበር፡- “እንደ የዋጋ ንረት ግብር ከሚልዮን ሰዎች አንዱ እንኳ ሳይገነዘብ ነባሩን ማህበራዊ አወቃቀር የሚያናጋ መሰሪ እርምጃ የለም”፡፡