የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሠ የሕወሃት ታጣቂዎች ወደ መኻል ሀገር እያመሩ በነበረበት ወቅት አንዳንድ የውጭ ኃይሎች አዲስ አበባን ለመቆጣጠር ወታደራዊ ኃይል አዘጋጅተው ነበር በማለት በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። ጀኔራሉ አክለውም፣ ወደ አዲስ አበባ እንዲገባ የተፈለገው ኃይል አንዳንድ ወገኖች በሀገሪቱ እናቋቁመዋለን ብለው ያሰቡትን ሽግግር መንግሥት የሚያግዝ ቅጥረኛ ወታደራዊ ኃይል እንደነበር እና እነዚሁ ኃይሎች ኢትዮጵያን የመበተን ጫፍ ላይ ደርሰው እንደነበር አውስተዋል። ከሕወሃት ጋር የሚደረገው ጦርነት ምዕራፍ አንድ ተጠናቀቀ እንጅ ጦርነቱ ገና እንዳልተጠናቀቀ የገለጹት ጀኔራሉ፣ መከላከያ ሠራዊት ትግራይ ገብቶ ሕወሃትን ከማጥፋት የሚያግደው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
“ሠራዊቱ የሚለካው በግዳጅ አፈፃፀሙ እንጂ በብሄሩ አይደለም!!”
=>> የኢትዮጵያ ሠራዊት የሚለካው በስራው ስኬት እና በግዳጅ አፈፃፀሙ እንጂ በብሄሩ አይደለም፤
=>> ከዚህ በፊት በነበረው የብሄር ተኮር የሠራዊት ግንባታ ዋጋ የከፈለው እራሱ ሠራዊቱ ነው፤
=>> ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ እና በሞያው ብቁ የሆነ ሠራዊት እየተገነባ ይገኛል፤
=>> በቅርቡ የተካሄደው ወታደራዊ የማዕረግ እና የሜዳይ ሽልማት በግዳጅ አፈፃፀም ላይ የተመሰረተ፣ በየደረጃው ላሉ እዞች ማዕረግ የተሰጠበት፣ የሠራዊቱ አመራሮችን የሚመጥን እና የሠራዊቱን ሞራል የገነባ ነበር፤
=>> በመጀመሪያው ምዕራፍ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የገጠመው የኢትዮጵያ ሠራዊት፤ ከጠላት የሰው ኃይል ቁጥር እና ትጥቅ ያነሰ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነትን ስንቁ ያደረገ ነበር፤
=>> ጦርነቱ ሲጀመር ከ250 ሺህ በላይ የታጠቀ የአሸባሪው ህወሓትን ኃይል ከነተጨማሪ ጀሌዎቹ ከ44 ሺህ ባልበለጠ ሠራዊት ነበር የገጠምነው፤
=>> ከአሸባሪው ህወሓት ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት አልተጠናቀቀም ያሉት ጀነራል አበባው ሠራዊቱ የምዕራፍ አንዱን ጦርነት አጠናቅቆ ለቀጣይ ግዳጅ እየተዘጋጀ ነው፤
=>> አሸባሪው ህወሓት ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ አካባቢዎች በማስወጣት የተገኘው ድል ህዝባዊ ድል ሲሆን፣ የጠላትን የማድረግ አቅም ያዳከመ እና ከፍተኛ የሰው ኃይል እና የንብረት ኪሳራ ያደረሰ ነው፤
=>> በጋሸና፣ በሚሌ እና በመሀል ግንባሮች ፈታኝ ውጊያዎች ተደርጓል፣ ሠራዊቱ ከፍተኛ ጀብዱ የሰራባቸው ግንባሮች ናቸው፤
=>> ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ የወሰደው ቁርጠኝነት የሠራዊቱን ዝግጁነት አቅም ያሳደገ መሆኑንም ጠቁመዋል።