አዲስ አበባ ሰላም ከሆነች ሌላው ቢጋይ ደንታ የሌለው መንግስት #ግርማካሳ

[addtoany]

ከታህሳስ 20 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 22 ባለው ጊዜ ብቻ በደራ ወረዳ ጮካና ድሬዳዳ ቀበሌዎች ከ33 በላይ ዜጎች በታጣቂዎች ተጨፍጭፈዋል፡፡ በባቡቡሬ ቀበሌ ቁጥራቸው ገና አልታወቀም እንጂ ብዙዎች እንደተገደሉ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ በአምቦ ዙሪያ 11 ዜጎች አማራዎች ናችሁ በሚል በታጣቂዎች ተገድለዋል፡፡በኖኖ ወረዳ 28 አማራዎች፣ 4 ኦሮሞዎች ፣ ሲደመር 32 ዜጎች በታጣቂዎች ተገድለዋል፡፡ሲደመሩ ቢያንስ 76 ዜጎች መሆናችው ነው፡፡

ይሄ እንግዲህ ከአዲስ አበባ አቅራቢያ ያሉ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በሸዋ ውስጥ እየሆነ ያለ ነገር ነው፡፡ በሙገር በመሳሰሉ ቦታዎች የመንግስት ተቋማትን፣ ፋብሪካዎችን ታጣቂዎች የተቆጣጠሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

እነዚህ ታጣቂዎች እነ ማን ናቸው ? የብልጽግና መንግስት በነጃል መሮ የሚመራው ኦነግ ሸኔ የሚላቸው ናቸው ይላል፡፡ ራሳቸውን ኦነሰ (የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወይም ኦላ Oromo Liberation Army) ብለው የሚጠሩት እነ ጃል መሮ፣ እኛ ንጹሃን ዜጎችን አንገድልም ፣ ብልጽግና ነው ይሄን የሚያደርገው ይላሉ፡፡ ማንም ይሁን ማንም እነ ጃል መሮ ይሁኑ ኦህዴድ ያደራጃቸው ታጣቂዎች ኦነጎች ናቸው፡፡ የኦነግን አርማ ይዘው፣ በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ፡፡ ስለዚህ ታጣቂዎችን የኦነግ ታጣቂዎች ነው የምላቸው፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ሆሎታ ካለው አካባቢ በቀር ዋና ከተማዋ አምቦ ከተማ ዙሪያ ያሉ፣ የአምቦ ዙሪያ ወረዳን ጨምሮ በሁሉም የኦሮሞ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን፣ በሁሉም አራቱ የወለጋ ዞኖች (ምስራቅ፣ ምእራብ፣ ሆሮ ጉድሩና ቄሌም) ፣ በስሜን ሸዋ ደራ፣ ኩዩ፣ ደገምና ሂዳቶ አቦቴ ወረዳዎች ፣ በአጠቃላይ ወደ 52 ወረዳዎች፣ መንግስት በአስተማማኝ ሁኔታ ሰላምና መረጋጋት አስፍኖ እያስተዳደረ አይደለም፡፡ የኦነግ ታጣቂዎች ያለምንም ችግር የሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡

ለምንድን ነው በሕወሃት ጊዜ አንድ ቀበሌ መቆጣጠር ያልቻለ ቡድን በዚህ መልኩ አምቦ አዲስ አበባ ደጃፍ ድረስ የመንቀሳቀስ አቅም ያገኘው ? ለምን ይሄንን ቡድን መቆጣጠር አልተቻለም ? ብዙዎች የሚጠይቁት ጥያቄ ነው፡፡

1ኛ በዶር አብይ አህመድ የሚመራው የብልጽግና መንግስት በጥቅሉ አገርን የማስተዳደር፣ ችግሮችን የመፍታት ብቃት ያለው ቡድን ስላልሆነ ነው።፡አስቀድሞ ችግሮችን ማወቅ የሚችል፣ ችግሮች እንዳይፈጠሩ አስቀድሞ ጥንቃቄዎችን የሚያደርግ፣ ችግሮች ሲፈጠሩ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆኑ ወዲያው መፍትሄ የሚፈልግ፣ በእቅድና በስትራቲጂ የሚንቀሳቀስ ጠንካራ የፌዴራል መንግስት ስለሌለ ነው፡፡ በፌዴራል መንግስቱ ውስጥ መስማማት የለም፡፡ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ከመስጠት የመደባበስ፣ የመሸፋፋን ባህል ነው ያለው፡፡

2ኛ የመንግስት አካል የሆነው የኦሮሞ ብልጽግናና የኦሮሞ ክልል መንግስት ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ከፍተኛ ፣ በርካታ መካከለኛና ታችኛ አመራሮችና አባላት ፣ ላይ ላዩን እንጂ ውስጥ ውስጡ ከኦነግ ጋር የሚሰሩ ናቸው፡፡ የኦነግ ታጣቂዎች አስፈላጊውን የስንቅ፣ የመሳሪያ የሎጂስቲክ ድጋፍ ከነዚህ የብልጽግና መንግስት አካላት በህብኡ ያገኛሉ፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ታጣቂዎችን ሲያደራጁ፣ ሲያሰለጥኑ የብልጽግና መንግስት የዞንና የወረዳ ሃላፊዎች እየታወቁና እየተደገፉ  ነው፡፡

3ኛ ብዙ የኦሮሞ ወጣቶች የኦነግን አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ ባይደግፉም፣ የብልጽግና መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በተለይም በኦሮሞ ክልል ሙሉ ለሙሉ በመዝጋቱ፣ ወጣቱ እንዲሸፍትና ወደ ጫካ እንዲገባ አድርገዉታል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ የአፈና አካሄድ በተዘዋዋሪ መንገድ ኦነግን ነው ያጠናከረው፡፡

4ኛ ኦነግ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በርካታ ጫካዎች፣ በረሃዎች አሉ፡፡ በዚያ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ከፍተኛ፣ በታማኝና ሃቀኛ መኮንኖች የሚመራ ወታደራዊ ስምሪቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ከአየር ኃይል፣ ከተወሰኑ ሜካናይድ ብርጌዶችና ክፍለ ጦሮች፣ ቀይ ባርኔጣ ለባሽ ኮማንዶዎች በስተቀር ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ብዙም አቅምና ጥንካሬ የለውም፡፡ አንዳንድ ቁል የመከላከያ ሃላፊዎችም ራሳቸው ኦነጎች እንደሆኑ ነው የሚነገረው። የኦሮሞ ልዩ ኃይል ሰለምና መረጋጋት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ግማሹ የልዩ ኃይል አባል በውስጥ ለኦነግ የሚሰራ ነው፡፡

ይህ የኦነግ እንቅስቃሴ የኦሮሞ ማህበረሰብን በመጥቀም ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ሳይሆን በተለይም አማራን በመጥላት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ኦሮሚያ የሚሉትን ኦሮምኛ ተናጋሪ ካልሆኑት የማጻዳት አላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ የዘር ጦርነት በአማራው ላይ የከፈተ፣ አማራውን እንደ ጠላት አድርጎ የሚወስድ አደገኛ እንቅስቃሴ ነው፡፡

እንደ አገር ለዚህ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ሲገባ በዶር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ነገሮች መደባበስና መሸፋፈንን ነው የመረጣው፡፡ ውሸትን ለህዝብ በመንገድ የህዝብን ሰቆቃ ዝም ብሎ ማየት ነው የመረጠው፡፡ አዲስ አበባ ስላም እስከሆነች ድረስ ለነርሱ ሌላው ቢጋይ ደንታ የላቸውም፡፡  ግን አንድ ያልተረዱት ነገር ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ከሌለ አዲስ አበባም አትኖርም።

See less