3 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ያጭበረበረው ግለሰብ ከአገር ሊወጣ ሲል ተያዘ

ከአምስት አመት በፊት ከተቀጠረበት ድርጅት 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በማጭበርበር የተጠረጠረው ግለሰብ በፌዴራል ፖሊስና በኢንተር ፓል ትብብር አቡዳቢ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በኮሚሽኑ የኢንተርፖል አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የተፈላጊ ሰዎች ክትትል ማስተበበሪያ ሃላፊ ኢንስፔክተር ዳኘ አድማሱ ፥ ተጠርጣሪው አናለም በተባለ የውጭ ኢንተርናሽናል ድርጅት በሂሳብ ሰራተኝነት ተቀጥሮ ሲሰራ በነበረበት ወቅት 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ በማጉደል መጠርጠሩን ተናግረዋል።

ተጠርጣሪው ይህንንም ተከትሎ ከሀገር ውጪ በመውጣት መሰወሩ የተገለፀ ሲሆን፥ የፌዴራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በመተባበር ለረጅም ጊዜ በፍለጋ ከቆየ በኋላ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አቡዳቢ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ ሀገር ቤት መመለሱን ተናግረዋል።

ሀላፊው ማንም ሰው ወንጀል ሰርቶ ከህግ ተሰውሮ መቅረት እንደማይችል በመግለፅ ኢንተርፖል እና የአቡዳቢ ፖሊስ ላደረገው ትብብር ምስጋና ማቅረባቸው ፋና ብሮድካስቲንግ ዘግቧል።