በአፋር ሰመራ የተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍን ለመበተን የክልሉ ልዩ ኃይሎች ወሰዱት በተባለ እርምጃ ሰዎች ተጎዱ

በአፋር ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ ሰመራ ከተማ ዛሬ የተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍን ለመበተን የክልሉ ልዩ ኃይሎች ወሰዱት በተባለ እርምጃ ቢያንስ 10 ሰዎች መጎዳታቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ገለጹ። በሰላማዊ ሰልፉ ከተሳተፉት ውስጥ ቢያንስ ሃምሳ ያህሉ ታስረዋልም ብለዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተሳተፉ፣ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የሰመራ ነዋሪ ዛሬ በከተማይቱ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ ወጣቶች ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተው እንደነበር ተናግረዋል። ሰልፈኞቹ “እንደሌላው የሀገሪቱ አካባቢ ሁሉ በአፋር ክልልም ለውጥ መደረግ አለበት” የሚል ጥያቄ እንደበራቸው ገልጸዋል። በህጋዊ እና ሰላማዊ መልኩ ሲካሄድ የነበረውን ሰልፍ የክልሉ ልዩ ኃይል እንደበተነው እና በወቅቱም በርካቶች መደብደባቸውን አስረድተዋል። በስድስት ሰልፈኞች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል።

የተጎዱት ሰላማዊ ሰልፈኞች በጭላሎ እና ዱብቲ ሆስፒታሎች ህክምናቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ የዓይን እማኙ ተናግረዋል። የታሰሩት ወጣቶች ደግሞ በአፋር ፖሊስ ኮሚሽን ቅጽር ግቢ ውስጥ እንዳሉ ገልጸዋል። የክልሉ ልዩ ኃይሎች አሁንም በከተማው እየተዘዋወሩ “ከሰላማዊ ሰልፉ ጀርባ አሉ ያሏቸውን ሰዎች በማደን ላይ ናቸው” ብለዋል።