በአሜሪካ የዲሞክራት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ዒላማው ያደረገው ቦምብ የላከው ግለሰብ እየታደነ ነው

BBC Amharic

ረቡዕ ዕለት ተቀጣጣይ ፈንጂ ይሆናሉ ተብለው የተጠረጠሩ ፖስታዎች ኒውዮርክ፣ ዋሺንግተን ዲሲ፣ እና ፍሎሪዳ መድረሳቸውን የደኅንነት ባለሥልጣኖች ተናግረዋል።

የአሜሪካ ፌደራል ወንጀል ምርመራ ፖሊስ እንዳስታወቀው ቦምቦቹ የተላኩት ለሒላሪ ክሊንተን፣ ለባራክ ኦባማ፣ ለቀድሞው የአሜሪካ የስለላ ተቋም ዳይሬክተር ጆን ብሬነን፣ ለቀድሞ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኤሪክ ሆልደር፣ ለካሊፎርኒያ ግዛት የዲሞክራቲክ ተወካይ ማክሲን ዋተርስ እና ሌሎች ነው።

ረቡዕ ዕለት የሲ ኤን ኤን ቢሮ ኃላፊ ዘንድ የተላከው ፓስታ በመድረሱ ሠራተኞች የኒውዮርክ ቢሮውን ለቅቀው እንዲወጡ ተደርጓል።

ለሒላሪ ክሊንተንና ለባራክ ኦባማ የተላከው ፖስታ ግን ለእነርሱ ከመድረሱ በፊት የደኅንነት አባላት እጅ ገብቷል።

ይህን ተከትሎም ለቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንደተላከ የታመነ ፖስታ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

ሁሉም ፖስታዎች በተመሳሳይ መልኩ የታሸጉና ከፍሎሪዳዋ የምክር ቤት አባል የተላከ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ምንም እንኳ ስማቸው ሲፃፍ ስህተት ቢኖርበትም ተወካይዋ ግን በዚህ ጉዳይ ስማቸው መነሳቱ ረብሿቸዋል።

 

ለሲኤንኤን የተላከው ቦምብ ምስል

ከዚህ በኋላ አንዳንድ የዲሞክራት ተወካዮች ዶናልድ ትራምፕ ባለፉት ጊዜያት ባካሄዷቸው ንግግሮች ጠብ በመቀስቀስ ወቅሰዋቸዋል።

የትራምፕ ደጋፊዎች በበኩላቸው “ይህ ቦምብ ዲሞክራቶች ምርጫ ለማሸነፍ የዶለቱት ሴራ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተደጋጋሚ ጋዜጠኞችን በተለይ ደግሞ ሲ ኤን ኤንን “ሐሰተኛ ዜና” እና “የሕዝብ ጠላት” በማለት ያወግዙ ነበር።

ባለፈው ሳምንትም ትራምፕ የምክር ቤት አባል የሆኑት ሪፐብሊካን አንድ ጋዜጠኛን አሽቀንጥረው በመጣላቸው ሰውየውን አሞካሽተዋቸው ነበር።

እስካሁን ድረስ ፖሊስ ስለተጠርጣሪዎቹ ምንም የሰጠው መረጃ የለም። ሆኖም አደን ላይ ነኝ ብሏል።

ይህ ጥቃት የተከሰተው አሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤትና የአካባቢ ሥልጣናት የመዳረሻ ምርጫ ሊካሄድ ሁለት ሳምንት ሲቀረውና የአሜሪካ ፖለቲካ በጦዘበት ጊዜ ነው።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሕዝቡ የሰለጠነ ፖለቲካን እንዲያራምድ፣ መገናኛ ቡዙኃንም ከጥላቻ ፖለቲካ ራሳቸውን እንዲቆጥቡ ጠይቀዋል።