የፀረ ሙስና ኮሚሽን የ450 የመንግሥት ባለስልጣናትና ሠራተኞችን ሃብት ለህዝብ ክፍት ሊያደርግ ነው

የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በመጀመሪያ ዙር የ450 የመንግሥት ባለስልጣናትና ሠራተኞችን ሃብት ለህዝብ ክፍት ለማድረግ የሶፍትዌር ሙከራ ላይ መሆኑን አሳውቋል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም እስካሁን የ150 ሺህ ባለስልጣናት እና የመንግስት ሠራተኞች ሃብት በመመዝገብ ለህዝብ ክፍት የማድረጊያ ሶፍትዌር ከህንድ ኩባንያ ጋር በመተባበር ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል።

የሶፍትዌር ትግበራው ለሙስና የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ የሆኑ ተቋማት ሃላፊዎችንና ሠራተኞችን ሀብት ይፋ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

እስካሁን የ80 ግለሰቦች የሀብት መረጃ ወደ ሶፍትዌሩ መመዝገባቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ የማሻሻያ ስራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን ተናግረዋል።

ሙከራው ሲጠናቀቅ ማንኛውም ግለሰብ የሚፈልገውን የሀብት ምዝገባ መረጃ በስነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ቢሮዎች በአካል ቀርቦ መመልከት እንደሚችልም ነው የጠቀሱት።

የሀብት ምዝገባ መረጃው ለህዝብ ክፍት የሚሆንበት ጊዜ ባይጠቀስም በቅርቡ እንደሚጀመር ግን ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ጠቁመዋል።

የሀብት ምዝገባ መረጃዎች እስከዛሬ ለህዝብ ክፍት ያልተደረገው ከስራው ውስብስብነትና በሶፍትዌሩ አለመጠናቀቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ላለፉት ዓመታት በሰው ሃይል እጥረት፣ በስራው ውስብስብነትና አቅም ማነስ ምክንያት የሀብት ማጣራት ስራ እንዳልሰራም ነው ኮሚሽነሩ ያነሱት።

አቶ አየልኝ በዘንድሮው በጀት ዓመት የ80 ግለሰቦች ሀብት እየተጣራ እንደሚገኝ ገልጸው ከዚህም ውስጥ የ23ቱ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ