ሕወሓት ለመሳሪያ ማከማቻነት እና ለጥፋት የሚጠቀምበት በመቐለ የሚገኘው መስፍን ኢንዱስትሪያል ላይ እርምጃ ተወስዷል

May be an image of skyየመከላከያ ሠራዊት ያካሄዳቸው የአየር ድብደባዎች ዒላማ ያደረጉት የህወሓት የጦር መሣሪያ ማምረቻ እና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎች ላይ ብቻ እንደሆነና ኢላማቸውን የመቱ መሆናቸው ተገለጸ፡፡ በመቐለ ከተማ የሚገኘው መስፍን ኢንዱስትሪያል የአሸባሪው ህወሓት የጦር መሳሪያ ማከማቻ፣ መስሪያ እና የከባድ መሳሪያዎች መጠገኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ታማኝ ምንጮች ነግረውናል።
እንደምንጮቻችን ገለጻ አሸባሪው ቡድን በመቐለ ከተማ የሚገኘውን የመስፍን ኢንዱስትሪያልን ሙሉ በሙሉ የመሳሪያ ማከማቻ እና ማምረቻ እንዲሁም የከባድ መሳሪያዎች የጥገና ማዕከል አድርጎ እየተጠቀመበት ነው።የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገጽ ባወጣው መግለጫ፤ የመከላከያ ሠራዊት ያካሄዳቸውን የአየር ድብደባዎች በተመለከተ የተዛባ ግንዛቤ ቢኖርም፣ በተቃራኒው ጥቃቶቹ ዒላማ ያደረጉት የህወሓት የጦር መሣሪያ ማምረቻ እና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎችን ብቻ ነው ብሏል። የመከላከያ ሠራዊት የሚያከውናቸው እነዚህ ሥራዎች የሽብር ድርጅቱ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን እና ሌሎች ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን ለመሸሸግ የሚጠቀምባቸውን እና ወደ ወታደራዊ መገልገያነት የቀየራቸውን የተወሰኑ ቦታዎች ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ያለመ ነው ሲልም አስታውቋል።
የኢፌዲሪ አየር ኃይል በመቐለ ከተማ የሚገኙና አሸባሪ ቡድኑ ለሽብር ተግባሩ የሚጠቀምባቸውን ስፍራዎች፣ እና መሳሪያዎች ላይ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል።
መከላከያ ሰራዊቱ በአየር ኃይሉ አማካኝነት በመቐለ ከተማ የሚገኙ የግንኙነት መሳሪያዎችን እና ታወሮችን የሽብር ቡድኑ ሲጠቀምባቸው መቆየቱን በማረጋገጥ እርምጃ የወሰደ ሲሆን ዛሬም የአስቸኳይ ጊዜ ማጣሪያ ባወጣው መረጃ የሽብር ቡድኑ ለመሳሪያ ማከማቻነት እና ለጥፋት ስራው የሚጠቀምባቸው አካባቢዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አረጋግጧል።