በምስራቅ ወለጋ የኦነግ ታጣቂ ቡድን በከፈተው ጥቃት ከ30 በላይ የአማራ ተወላጆች ተገደሉ

በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ በሃሮ አዲስአለም ቀበሌ የኦነግ ታጣቂ ቡድን ዛሬ በከፈተው ጥቃት የሞቱ የአማራ ተወላጆች ቁጥር ከ30 ማለፉን በአካባቢው ያሉ የአማራ ተወላጆች ለኢትዮ 360 ገለጹ። እስካሁም የቆሰለው ሰው ምን ያህል እንደሆነ ባይታወቅም ነገር ግን ጉዳት የደረሰባቸውን ቁስለኞች ወደ ህክምና መውሰድ ባለመቻሉ ህይወታቸው እያለፈ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
እስካሁን ድረስ ተኩሱ አለመቆሙን የሚናገሩት የአማራ ተወላጆች ከቀናት በፊት ያለምንም ማስጠንቀቂያ ልዩ ሃይሉን ከአካባቢው እንዲወጣ ያደረገው የአካባቢው አመራር ዛሬ እየተካሄደ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስቆም ምንም አይነት ሙከራ አለማድረጉንም አመልክተዋል። ኢትዮ 360 ለተከታታይ ወራት ከ60ሺ በላይ ተፈናቃይ የሚገኝባቸውን የሃሮአዲስአለምና የባጊን ቀበሌዎች በዚሁ ገዳይ ቡድን መከበባቸውንና ንጹሃን ዜጎችም የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ መሆኑን ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል።
መንገድ አፍርሶና መውጫ እንዳይኖር አድርጎ የአማራ ተወላጆችን ከቦ እየገደለ ያለው ቡድን ከፌደራል ጀምሮ እስከታች ባለው አመራር የሚደገፍ መሆኑ ደግሞ ነገሮችን የበለጠ እንዲከፉ ማድረጉን የአማራ ተወላጁ በተደጋጋሚ ለኢትዮ 360 ሲገልጹ ቆይተዋል። ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ቢሆንም እስካሁን ግን የደረሰላቸው አንድም አካል አለመኖሩን ይናገራሉ። ይሄ ዜና እየተጠናቀረ ባለበት በዚህ ሰአትም በንጹሃን የአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት እንደቀጠለ ነው። (ኢትዮ 360)