ጀርመን እና ፈረንሳይ ከሌሎች የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በመሆን ዶ/ር ቴድሮስን ለሁለተኛ ጊዜ እጩ አድረገው አቅረበዋል

የአውሮፓ ሀገራት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ለሁለተኛ ጊዜ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እንዲሆኑ ድጋፋቸውን ሰጡ፡፡
በጀኔቭ መቀመጫው ያደረገው የጀርመን ቋሚ ሚሽን (Germany UN Geneva) “ጀርመን እና ፈረንሳይ ከሌሎች የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በመሆን ዶ/ር ቴድሮስን ለሁለተኛ ጊዜ እጩ አድረገው አቅረበዋል” ሲል በትዊተር ገጹ ላይ አጋርቷል፡፡ እስካሁን 17 የአውሮፓ ሀገራት ለዶ/ር ቴድሮስ ድጋፋቸውን መስጠታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ዶክተር ቴድሮስ እስካሁንም እጩ የመሆን ፍላጎት ይኑራቸው አይኑራቸው ግልፅ ባያደርጉም ሀገራቱ ግን ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሮይተርስ ስቴት ኒውስን ዋቢ በማድረግ ከወራት በፊት እንደዘገበው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም የድርጅቱን ሀላፊ ሆነው ለቀጣይ አምስት አመታት ለምምራት በሚያስችላቸው የሁለተኛ ዙር ውድድር ለመሳተፍ ፍላጎት አላቸው ብሎ ነበር፡፡ ከቀናት በፊት ባወጣው ዘገባም ከዶ/ር ቴድሮስ ውጭ የቀረበ እጩ እንደሌለና ብቸኛ እጩ ሆነው መቅረባቸው ሪፖርት አድርጎ ነበር። ኡጋንዳ ሌሎች ከደገፉት እደግፋለሁ ስትል ኬንያ ሙሉ ድምጼ ከዶክተር ቴድሮስ ጋር ነው ማለቷም የሚታወስ ነው፡፡
በዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት እጪነትን በማስመልከት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ግጭት ጉዳይ ዋና ዳይሬክተሩን ለቀድሞ ድርጅታቸው ህወሀት በመወገን የዲፕሎማሲ ድጋፍ አድረገዋል በማለት ሲከሳቸው ቆይቷል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ በበኩላቸው “እኔ ለማንም አልወግንም ውግንናየ ለሰላም ነው” በማለት በወቅቱ ምለሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡በዚህ የተነሳ ዶ/ር ቴድሮስ እንደፈረንጆቹ ግንቦት 2022 በጀኔቭ በሚደረገው ምርጫ ከትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ድጋፍ ሊያጡ እንደሚችሉ ይነሳል፡፡

የአፍሪካ ህብረት በተመሳሳይ በጉዳዩ ላይ አስካሁን አስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡በፈረንጆቹ በ2019 መገባደጃ ላይ አዲሱ የ SARS-CoV-2 ቫይረስ በማዕከላዊ ቻይናዊቷ ውሃን ከተማ መከሰቱን ተከትሎ የዓለም የጤና ድርጅት ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመታገል በሚያደርገው ትግል ዶ/ር ቴድሮስ ጎልተው ወጥተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ዋና ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፤ ኮሮና ዓለም አቀፍ ወረርሺኝ ነው ተብሎ ከመፈረጁ በፊት በወርሀ ጥር 2020 ወደ ቻይና እቅንተው ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር በትብብር ለመስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች መምከራቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ይህ አካሄድ በቀድሞ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አልተወደደላቸውም ነበር፡፡ ዶናልድ ትራምፕ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስን “አፍቃሬ-ቻይና” ናቸው በሚል ክስ፤ አሜሪካ በድርጀቱ የነበራትን ሚና እንድትገታ ውሳኔ አሳልፈው እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡ ምንም እንኳ አሁን ላይ የትራምፕ ውሳኔ በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን ቢቀለበስም፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ የኢትዩጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የወባ በሽታ ፣ ኤች አይ ስረጭት እንዲሁም የእናቶች እና ጨቅላ ህፃናት ሞት እንዲቀንስ በሰሩት ስራ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡