ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ስድስት ዕድሜያቸው ከ5 አመት በታች የሆኑ ሕፃናት በረሐብ ምክንያት ሞተዋል – መቐለ አይደር ሆስፒታል

DW : ግርማነሽ መለስ በትግራይ ክልል ከሚገኘው ከእንድርታ ወረዳ በረሐብ ክፉኛ የተጎዳ የአንድ አመት ከስድስት ወር ሕፃን ይዛ ወደ አይደር ሆስፒታል ያቀናችው ለልጇ ምግብ ከተገኘ በሚል ተስፋ ነበር። “አይደለም ሕፃን ልጅ እኛም ብንሆን የነበረን ስለተዘረፈ ካገኘን እንበላለን ከሌለ ጦማችንን ነው የምናድረው” ስትል ለመቀሌው ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ የተናገረችው ግርማነሽ ግን በሆስፒታሉ ብቻዋን አይደለችም።

ሰውነቱ የሳሳው፣ አይኑ የጎደጎደው እና የቆዳ መገርጣት የሚታይበት የአራት ዓመቱ ክብሮም ፈቃዱ በዚያው በአይደር ሆስፒታል ይገኛል። አባቱ አቶ ፍቃዱ ገብረእግዚዓብሔር በጦርነቱ ምክንያት ከእጅ ወደ አፍ የነበረ ኑሯቸውን መሙላት ተስኗቸው ለርዳታ ጠባቂነት መጋለጣቸውን ተናግረዋል።

“በየቤቱ የምግብ እጥረት አለ። ሕፃናት ሊመገቡት የሚችሉ ወተት ይሁን አምባሻ ወይም ሌላ ነገር የለም። እንደ አባት የቀን ሥራም ቢሆን ሠርተን ገንዘብ አግኝተን ቤተሰብ እንዳንመራ ሥራ የለም። እጃችንን እና እግራችንን አጣጥፈን ቁጭ ብለን ነው ያለንው” ሲሉ አቶ ፍቃዱ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ስድስት ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሕፃናት በረሐብ ምክንያት መሞታቸውን የሚገልጽ መረጃ ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ መቐለ ከተማ ከሚገኘው አይደር ሆስፒታል ማግኘቱን ዘግቧል። በአይደር ሆስፒታል መረጃ መሠረት በተመሳሳይ ጊዜ 111 ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ በረሐብ የተጎዱ ሕፃናት ለሕክምና ወደ ሆስፒታሉ አቅንተዋል። በትግራይ ሽረ፣ ቆላ ተምቤን፣ ኦፍላ፣ ሓውዜን እና ሌሎች አካባቢዎች በረሀብ ምክንያት ሞት መከሰቱ የክልሉ አስተዳደር ዐስታውቋል።