ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ የአቋም መግለጫ

ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ

ጥቅምት 2 ቀን 2011 ዓ.ም.

የህዝብ አገልጋይ መንግሥታዊ ተቋማትን ለመገንባት እየተደረገ ላለው ጥረት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል!

አዲሱን ዓመት በአዲስ የለውጥ መንፈስ በመቀበልና በዋና ዋና የዓመቱ ትኩረቶች ላይ መሠረት ያደረገውን የኢፌድሪ የመንግስት አቅጣጫዎች በሳምነቱ መጀመሪያ በግልፅ መገንዘብ መቻላችን ግልጽ ነው፡፡

በእርግጥ ለበርካታ ዓመታት በአገራችን የታዩ ኢፍትሃዊና ኢዲሞክራሲያዊ አሰራሮች መቀጠል እና የኢፌዴሪ መንግሥት የህዝቡን መሰረታዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ የተከተለው ዘገምተኛ አካሄድ በአገራችን ሰላምና መረጋጋት ብሎም በህልውናዋ ላይ አስከትሎት የነበረውን ከባድ ችግር ሁላችንም የምንገነዘበው ነው።

የችግሩን መሰረታዊ መንስኤዎች እና መፍትሄዎች በጥልቀት በመመርመር አዳዲስ የለውጥ እርምጃዎችን በመውሰዱ ዛሬ በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማየት የጀመርንበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡

አሁንም ቢሆን የአገራችን ሰላምና ህልውና በአስተማማኝ መልኩ ሊረጋገጥ የሚችለው ሕዝባችን በተደጋጋሚ ሲያነሳቸው የነበሩ የልማት፣ የፍትህ፣ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲ፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአግባቡ ሲመለሱ ብቻ መሆኑን የኢፌዴሪ መንግሥት በጥብቅ ይገነዘባል። ያጋጠሙንን ችግሮች በዘለቄታው መፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ለምርጫ የማይቀርብ ጉዳይ መሆኑንም ከልብ ያምናል።

ከዚህ በመነሳትም የሕዝባችንን ጥያቄዎች ለመፍታት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት መንግሥት የጀመረውን አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተቋማዊ ቅርጽ ለማስያዝ እየተንቀሳቀሰ ያለበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።
የተመዘገቡትን የለውጥ ውጤቶች ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ አገራዊ የሪፎርም ሥራዎችን ማካሄዱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

እያከሄዳቸው ካሉት በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መካከልም አንዱ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን አደረጃጀት እና አሰራር ማሻሻል ሲሆን ሕዝብን በግልጸኝነት እና በቅንነት ማገልገል ዓላማቸው ያደረጉ የመንግሥት ተቋማትን ለመገንባት ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ተቋማቱ እርስ በርስ ተናበው እና ተቀናጅተው የሚሰሩ፣ የሕዝብ ሀብትን በቁጠባ የሚጠቀሙ እና ውጤታማ አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ይሆኑ ዘንድ አስፈላጊውን የህግ፣ የተቋማት እና የአሰራር ማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።

በመሆኑም የሕዝባችንን ጥያቄዎች በአስተማማኝ መልኩ ለመመለስ የሚያስችሉንን ስትራቴጂያዊ የለውጥ እርምጃወች እየወሰድን ባለንበት በአሁኑ ወቅት ተስፋ ሰጪው ለውጥ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መላው ህዝባችን እና ዜጎቻችን የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ፣ በተለይም ለአገራዊ ለውጡ ቀጣይነት መሰረት ለሆነው ሰላማችን እንደወትሮው ሁሉ ዘብ ሆነው እንዲቆሙ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።