በሻሸመኔ ከተማ ሰው በመግደልና ዘቅዝቆ በመስቀል ወንጀል የተጠረጠሩ 14 ግለሰቦች ክስ ሊቀርብባቸው ነው

በሻሸመኔ ከተማ ሰው በመግደልና ዘቅዝቆ በመስቀል ወንጀል የተጠረጠሩ 14 ግለሰቦች በቁጥጥር ስል አውሎ በስድስቱ ላይ ክስ እንደሚመሰርት የከተማው ፓሊስ መምሪያ አስታወቀ።ግለሰቦቹ ነሃሴ 6 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዳይሬክተር አቶ ጃዋር መሀመድ አቀባበል ስነ ስርዓት ላይ ግርግር በመፍጠር አንድ ግለሰብን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ በመስቀል ወንጀል ጠርጠራቸውን የአቃቤ ህግ መዝገብ ይጠቁማል።

የከተማው ፓሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር መኮንን ታደሰ እንደተናገሩት፥ ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል በስድስቱ ላይ አቃቤ ህግ ክስ ለመመስረት የሚያስችል በቂ ማስረጃ በማግኘቱ ክስ ለመመስረት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።ተጠርጣሪዎቹ በዛሬው እለት በሻሸመኔ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት እንደሚቀርቡም አስታውቋል።ነሃሴ 6 ቀን 2010 ዓ.ም በተፈጠረው ግርግርና ግፊያ የ3 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ የከተማው ፓሊስ ተሽከርካሪ ቃጠሎ እንደደረሰበት ጠቅሶ ኤፍ.ቢ.ሲ ዘግቧል።