ጥቅምት 1 ቀን ትምሕርት ይጀመራል፤ የትምሕርት ፕሮግራሙ ይፋ ተደርጓል ።

በመዲናዋ የ2014 ትምህርት ዘመን ፕሮግራም ይፋ ተደረገ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የ2014 ዓ/ም የትምህርት ካላንደርን ይፋ ያደረገ ሲሆን ከጥቅምት 1 ቀን ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ትምህርት እንደሚጀምር ተገልጿል።

ከጥቅምት 1 በፊት ፤ ከመስከረም 24 እስከ 28 ድረስ የትምህርት ሳምንት እንደሚካሄድ ተገልጿል። ሁሉም መምህራን እስከ መስከረም 18 ድረስ ሪፖርት ያድርጉ ተብሏል።

የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ትምህርት 99 ቀናት ሲሆን የማጠቃለያ ፈተናው ከየካቲት 14 እስከ የካቲት 18 ድረስ እንደሚሠጥ ተገልጿል።

የሁለተኛው መንፈቅ ዓመት ትምህርት ከየካቲት 28 እስከ ሀምሌ 15 ይሰጣል ተብሏል፤ ይህም መንፈቅ በተመሳሳይ 99 የትምህርት ቀናት አሉት።

የ8ኛ ክፍል ፈተና በወቅቱ ሲወሰን ለሶስት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን የማስፈተኛ ጣቢያ የሆኑ ትምህርት ቤቶች ብቻ ዝግ ይደረጋሉ ፤ በተመሳሳይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና የሚሰጥበት ቀን ተወስኖ ሲሰጥ ለ2013 እና ለ2014 ለእያንዳዳቸው 4 ቀናት የመፈተኛ ናቸው፤ የማስፈተኛ ጣቢያ የሆኑ ትምህርት ቤቶች ብቻ ዝግ ይደረጋሉ ተብሏል።

የሁለተኛው መንፈቅ ዓመት ትምህርት የማጠቃለያ ፈተና ከሰኔ 30 እስከ ሃምሌ 5 ድረስ የሚሰጥ ሲሆን የ2014 ትምህርት ዘመን ሃምሌ 15/2014 በየትምህርት ቤቱ በመዝጊያ ስነስርዓት የትምህርት ማስረጃ ሰርተፊኬት በመስጠት ይጠናቀቃል።