ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክን ዛሬ መርቀው ከፈቱ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክን ዛሬ መርቀው ከፈቱ፡፡

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ተጋባዥ እንግዶች ተግኝተዋል፡፡

ግንባታው በ2009 ዓመተ ምህረት ጥቅምት ወር ላይ የተጀመረው ይህ ፓርክ፤ በ102 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ከ4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ነው ግንባታው የተካሄደው፡፡

ፓርኩ በተለያየ ዘርፍ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች የሚያገለግሉ 19 የመስሪያ ሼዶችን የመስሪያ ቦታዎችን የያዘ ነው።

ከእነዚሀ ሼዶች ውስጥም ስድስቱ በ11 ሺህ ካሬ ሜትር፣ ዘጠኙ በ5 ሺህ 500 ካሬ ሜትር፣ አራቱ ደግሞ በ3 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፉ ናቸው።

ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባም ከ60 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምረቃ ስነስርዓት ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰዱ አንኳር ነጥቦች፡-

• የኢንዱስትሪ ልማት የአገራችንን ጎስቋላ ገፅታ የሚለውጥ ነው፡፡

• ግብርና እንዲዘምንና በሂደትም ለኢንዱስትሪ መሪነቱን እንዲለቅ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው፡፡

• መንግስት ለኢንዱስትሪ ልማት ትኩረት ሰጥቷል፡፡

• በዘርፉ ተጨባጭና ፍሬያማ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡

• የተመቻቸ የኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሀብቶች በአጭር ጊዜ ስራ እንዲጀምሩ ያስችላል፡፡

• የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፋና ወጊ ከሆኑት መካከል ነው፡፡

• በጨርቃጨርቅና አልባሳት ስፔሺያላይዝ ያደረገ ፓርክ ነው፡፡

• ለባቡር፣ አየር፣ የብስ ትራንስፖርት ቅርበት ያለው ከተማ ነው አዳማ፡፡

• ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል፣ የአርሶ አደሩን ገቢም የሚያሻሽል ፓርክ ነው፡፡

• በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ ሲጀምር ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል፡፡

• የቴክኖሎጂ ሽግግር የጥናትና ምርምር ማዕከል ይሆናል ፓርኩ፡፡

• የላቀ የብቃት ማዕከል እንዲሆን እንሰራለን፡፡

• ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ተደራጅተው ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ግብዓት እንዲያቀርቡ ይመቻችላቸዋል፡፡

• የክልሉ መንግስት ለአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ዶ/ር አርከበ ዑቁባይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምረቃ ስነስርዓት ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰዱ አንኳር ነጥቦች፡-

• የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ2000 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ያረፈ ፓርክ ነው፡፡

• ከሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና ከሌሎች ቀደም ሲል ከተሰሩት ፓርኮች ልምድ ተቀምሮ የተሰራ ነው፡፡

• በዋናው የኢትዮ-ጅቡቲ የኤክስፖርት ኮሪዶር ላይ የሚገኝ ፓርክ ነው፡፡

• ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚስተናገዱበት ፓርክ ነው፡፡

• ከአፍሪካ ትላልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አንዱ ነው፡፡

• ኢትዮጵያ በ2012 በድምሩ 30 ፓርኮች ይኖሯታል፡፡

• በኢንዱስትሪ ፓርኮች የኃይል አቅርቦት እጥረት ስላለ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት፡፡

• በዘርፉ የሰው ኃይል ልማትም ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

• የአዳማና አካባቢው ወጣቶችና ነዋሪዎች ፓርኩን እንደ ዓይናቸው ብሌን ሊጠብቁት ይገባል፡፡

• ለዚህ ፓርክ ልማት ተነሺዎች የስራ ዕድል መፍጠር መንግስት ያስቀመጠው አቅጣጫ በመሆኑ ይህንኑ አቅጣጫ ይዘን እንሰራለን፡፡