ልደቱ ከሚለው ባሻገር;
ቀስተ-ደመና የተመሠረተው “የመኢአድን እብጠት ለማስተንፈስና ኢ/ር ኃይሉ ሻወልን ከጨዋታው ገለል ለማድረግ” ነበር። ለዚህም መነሻ ምክንያት ነበረው። ቀስተ-ደመና ከመቋቋሙ ቀደም ብሎ ተቃዋሚዎችን; በተለይ የያኔውን መኢአድና ኢዴአፓን ለማዋሃድ አራት ታዋቂ ምሁራን ከላይ እታች ይሉ ነበር። በሥም ለመጥቀስም ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም; ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ; ዶ/ር በፈቃዱ ደግፌና ጠበቃ አበበ ወርቄ ነበሩ። ሆኖም ግን በተለይ በኢ/ር ኃይሉ ሻወል እንቢተኝነት (በነሱ እይታ) ጥረታቸው ሊያፈራ ባለመቻሉ ቀስተ-ደመናን ለመመሥረት ተገደዱ።
የቀስተ-ደመና መሥራታ ሌሎች ገፊ ምክንያቶች ቢኖሩትም በወቅቱ “ከሚገባው በላይ ራሱን ይኮፍሳል” ብለው የሚገምቱትን የመኢአድን ድርጅታዊ እብጠት ማስተንፈስና መሪውን ኢ/ር ኃይሉን ከጨዋታው ገለል ማድረግ የሚል ግብ ነበረው። የዚህ ፕሮጀክት ዋነኛ ተባባሪ ደግሞ የያኔው ኢዴአፓ; በተለይም እነልደቱ አያሌው ነበሩ። በወቅቱ ኢንጅነር ኃይሉ የቅንጅቱ ሊቀ-መነበር እንዳይሆኑ ተቃውሞ የቀረበባቸው በተለይ “አማራ ናቸው” በሚል ነበር። ኢ/ሩም ይህን ለመከላከል “ዘሬ ቢቆጠር 75% ኦሮሞነት አለብኝ” የሚል ሙግት አቀረቡ። ትናንትና “የዚህን ምክንያት አሁን አትጠይቁኝ” ብዬ ነበር። ዳሩ ግን “በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ አቶ ልደቱ “የተጠቃሁት በአማራነቴ ነው” ማለቱ ዝምታዬን ፈነቀለው።
እውነቱን እናውራ ከተባለማ ከቅንጅት ምሥረታም በፊት; በተለይ በመኢአድና ኢዴአፓ መካከል ተጀምሮ የነበረው ድርድር ሲቋረጥ እነልደቱ በአደባባይ “መኢአድ ከስያሜው ጀርባ የአማራ ስብስብ የያዘ ኃይል ነው” የሚል ቅስቀሳ አድርገዋል። በወቅቱ የተሰጡት መግለጫዎች ያኔ በወጡት ጋዜጦች ወጥተዋል; በእጃችንም ይገኛሉ። ይሁንና ዛሬ ላይ አቶ ልደቱ እጥፍ ብሎ “የጥቃት ሰለባ የሆንኩት በአማራነቴ ነው” ማለቱ የሚያስተዛዝብ ብቻ ሳይሆን የሚያነጋግርም ነው።
ይኸ ማለት ግን ልደቱ እውነት የለውም ማለት አይደለም። በሌላ አነጋገር ልደቱ እውነቱን ገልብጦ መናገሩ የዶ/ር ብርሃኑ ነጋንም ሆነ የሌሎቻችንን ጉድፍ አያጠራውም። ለዚህም ነው በዚያ ሂደት ውስጥ የነበርንና አሁን በህይወት ያለን ሰዎች ቁጭ ብለን በጥሞና እንድንነጋገር በተደጋጋሚ ስወተውት የነበረው። አለበለዚያ ግን በተናጠል መካሰስና መጠላለፍ ነው የሚሆነው።
አሁንም አልረፈደም።