ኦነግ አገር ውስጥ ካሉት ከ4,000 በላይ ወታደሮች ከግማሽ በታች ብቻ ትጥቅ ፈተዋል

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አገር ውስጥ ከሚገኙ ወታደሮቹ ውስጥ 1,500 ያህሉ ብቻ ትጥቅ ፈተው መንግሥት ወዳዘጋጀው ካምፕ መግባታቸው ተገለጸ፡፡

ኦነግ በአጠቃላይ ከ4,300 በላይ ወታደሮች እንዳሉት፣ ከእዚህም ውስጥ 1,500 ብቻ ትጥቅ መፍታታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኢብሳ ነገዎ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አሁንም ትጥቅ ያልፈቱ ወታደሮች አሉ፡፡

‹‹አገር ውስጥ ለመምጣት ስንወስን በአዎንታዊና ሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ነው፤›› ብለው፣ በአሁኑ ጊዜ ትጥቅ የፈቱት 1,500 ወታደሮች ሻሸመኔ በሚገኝ ካምፕ እንደሚገኙ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

ከቀናት በፊት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፣ ኦነግ አሁንም አስታጥቆ እያንቀሳቀሰ ያለውን ጦሩን በአስቸኳይ ትጥቅ እንዲያስፈታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

ኃላፊው በግል የፌስቡክ ገጻቸው በኦሮሚኛ ቋንቋ ባሠፈሩት ጽሑፍም ግንባሩ ወታደሮቹን ትጥቅ አስፈትቶ በአስቸኳይ መንግሥት ወዳዘጋጀለት ካምፕ እንዲያስገባ አሳስበው ነበር፡፡

ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት ሌላው የኦነግ አመራር አቶ ቶሌራ አደባ፣ አሁንም በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች የታጠቁ የኦነግ ወታደሮች እንዳሉ አምነው፣ ድርጅታቸው በአፋጣኝ ትጥቅ ለማስፈታት ከመንግሥት ጋር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡