በምዕራብ ጎንደር መተማ ደለሎ አካባቢ ተፈጠረ በተባለው የድንበር ውዝግብ ብአዴን ቁርጠኛ አቋም እንዲይዝ ተጠየቀ።

በምዕራብ ጎንደር መተማ ደለሎ አካባቢ ተፈጠረ በተባለው የድንበር ውዝግብ ብአዴን ቁርጠኛ አቋም እንዲይዝ ከጉባኤተኞች መነሳቱን የጉበኤው ቃል አቃባይ አቶ ምግባሩ ከበደ ገለፁ

ከተጀመረ ሁለተኛ ቀኑን የያዘው 12ኛው የብአዴን ድርጅታዊ ጉባኤ ትናንት በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ሲያደርግ መዋሉን የጉባኤው ቃል አቀባይ አቶ ምግባሩ ከበደ ገልፀዋል፡፡

እንደ ቃል አቀባዩ ገለፃ በዛሬው የጉባኤው ውሎ ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ተነስተዋል ነው ያሉት፡፡

ከህግ የበላይነት ጋር በተያያዘ የክልሉን ህዝብ ሰላም ማስጠበቅ የብአዴን የቤት ስራ መሆኑን ጉባኤተኛው ጠንከር ያለ አቋም መያዙንም ገልፀዋል፡፡

ከአማራ ክልል የወሰንና ድንበር ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሰፊ ውይይች ተደርገዋል ያሉት አቶ ምግባሩ፤ በተለይም በምዕራብ ጎንደር መተማ ደለሎ አካባቢ ተፈጠረ በተባለው የድንበር ውዝግብ ብአዴን ቁርጠኛ አቋም እንዲይዝ በጉባኤተኛው መነሳቱም ተገልጿል፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በወልቃይት፣ ጠገዴና ፀገዴ፣ በራያ አካባቢ የተነሱ የማንነት ጥያቄዎች ላይ ብአዴን ጠንከር ያለ አቋም በመያዝ ችግሮቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ከጉባኤተኞች ተነስቷል፡፡

በተነሱ ጥያቄዎች ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ እየሰጡ እንደሆነ ቃል አቀባዩ ገልፀዋል፡፡

እስከ ድርጅቱ ጉባኤ ድረስ ታግደው የነበሩ አባላት እንዲገኙ ጥሪ ተላልፎ እንደነበር የገለፁት ቃል አቀባዩ የተወሰኑት አባላት ተገኝተው የታገዱበት ሁኔታ አግባብ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጥሪ ከተደረገላቸው የታገዱ አባላት ውስጥ የተወሰኑት ያልተገኙ ቢሆኑም የዴሞክራሲ ምህዳሩን ላለመጉዳት በሌሉበት የታገዱበት ጉዳይ ለጉባኤተኛው ግልፅ ተደርጓል ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡

በቀጣይም ጥፋተኛ ሆነው በተገኙ አባላት ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

ውይይቱ በነገው ዕለትም ሲቀጥል ያላለቁ ጉዳዮችን ቋጭቶ ወደ ሚቀጥለው ርዕሰ ጉዳይ እንደሚገባ ይጠበቃል ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡

ምንጭ፡- አማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን