ለቀውስ የዳረገን የጎሳ ፖለቲካ ተወልዶ፣ አድጎ፣ ጎልሞሶና አርጅቶ ተፈጥሯዊ ሞት ሞቷል – ወጣቶች ከጎሳና ብሄር አስተሳሰብ ወጥተው ለኢትዮጵያውነት መቆም አለባቸው – አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን

ላለፉት ቀላል ለማይባሉ ዓመታት አገራችንን አስጨንቆ የያዛትና አሁንም ላለችበት ቀውስ የዳረጋት የጐሳ ፖለቲካ አሳብ እንደማንኛውም ፍልስፍናና ሀሳብ ተወልዶ አድጐ አርጅቶና በስብሶ ተፈጥሯዊ ሞቱን ሞቷል

ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)

May be an image of 4 people and people standingወጣቶች ከጎሳና ብሄር አስተሳሰብ ወጥተው ለኢትዮጵያውነት መቆም አለባቸው ሲል የክብር ዶክትሬት ሽልማቱን ከጎንደር ዩንቨርስቲ በዛሬው እለት የተሸለመው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

የክብር ዶክትሬት ሽልማቱ የዪንቨርሲቲ ሴኔት በወሰነው መሰረት የሂዩማን ሊትሬቸር የክብር ዶክትሬት ሽልማቱን በ6 ሺህ 5መቶ 74 ተማሪዎችን ፊት ተቀብሏል።

አርቲስት ቴዲ አፍሮ በመድረኩ ላይ ባደረገው ንግግር ዪንቨርሲቲውን አመስግኖ ለተመራቂ ተማሪዎች የእንኳን ደስ ያላቸሁ መልዕክቱን ያስተላለፈ ሲሆን ወጣቶች ከጎሳና ብሄር አስተሳሰብ ወጥተው ለኢትዮጵያውነት እንዲቆሙ ጠይቋል ።

ከክብር ዶክትሬት ሽልማቱ በተጨማሪም አርቲስት ቴዲ አፍሮና ባለቤቱ አምለሰት ሙጬ ከጎንደር ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን የክብር ካባ ተበርክቶላቸዋል ።


የክብር ዶክተር ቴዲ አፍሮ መልዕክት

May be an image of 4 people, people standing and outdoorsበታሪካዊዋና በገናናው ጀግና ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የትውልድ ሃገር በሆነችው የጐንደር ከተማ በተዘጋጀው በዚህ የምረቃት መርሀ ግብር ላይ የታደማችሁ ጥሪ የተደረገላችሁ ክብሯን እንግዶች ክቡራትና ክብሯን በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬን እያቀረብኩ በተለይ በዛሬው እለት ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ ፍሬያችሁን ለማየት ለበቃችሁ ተመራቂዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ የሚል መልክቴን ላስተላልፍ እወዳለሁ

በመቀጠልም በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ከጉኔ ሳይለየኝ ያለ መታከት የረዳኝ ቅዱስ እግዚአብሔርን በታላቅ ትህትና ለማመስገን እወዳለሁ

እንዲሁም በተሰማራሁበት የኪነ ጥበብ ዘርፍ ይህ የክብር ሽልማት ይገባሃል ብሎ በዛሬው እለት በእናተ ፊት እንድቆም ምክንያት ለሆነኝ ለአንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርስቲ ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ

በማስከተልም የሕይወት አጋሬ ለሆነችዉ ባለቤቴ አምለሰት ሙጬ እና ለወላጅ አባቴ አቶ ካሳሁን ግርማሞ እንዲሁም ለወላጅ እናቴ ለወ/ሮ ጥላዬ አራጌና ለመላው ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ ከፍያለ የአክብሮት ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ

ከእዚህ በማስከተልም በማስተላልፈው አጭር መልክት ንግግሬን እቋጫለው

ሃገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የገባችበት ከባድ አጣብቂኝና እጅግ ፈታኝ ሁኔታ በሁሉም ዘንድ የታቀወቀ ቢሆንም እንኳን ነገርግን እናት ከመጨረሻው አስጨናቂ ምጥ በኋላ አዲስ ልጇን አይታ እንደምትደሰተው ሁሉ ሃገራችንም ከገጠማትና ሊገጥማት ከሚችለው ማንኛውም ከባድ አደጋ በደል ወጥታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም
ላለፉት ቀላል ለማይባሉ ዓመታት አገራችንን አስጨንቆ የያዛትና አሁንም ላለችበት ቀውስ የዳረጋት የጐሳ ፖለቲካ አሳብ እንደማንኛውም ፍልስፍናና ሀሳብ ተወልዶ አድጐ አርጅቶና በስብሶ ተፈጥሯዊ ሞቱን ሞቷል

ሰለዚህም ከዚህ በኋላ መላው የሃገራችን ህዝብ በተለይም በተለይም ወጣቶች በጎሳና በዘር እንዲሁም በሃይማኖት ልዩነት ሳትናወጡ ከመቼው ጊዜ በላይ በአንድነትና በፍፁም ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ስሜት በተጠንቀቅ ፀንታችሁ መቆም ያለባችሁ ወይም ያለብን መሆኑን በአፅኖት ለማሳሰብ እወዳለሁ

እኛ የአዲስቷ የኢትዮጵያ ትንሣኤ የአባቶቻችን ልጆች ኃይላችን ጉልበታችን እና መመኪያችን ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው

ራዕያችንም ፍቅር ሠላምና ፍትህ የሰፈነባት
ታላቅ እና ገናና አንዲት ኢትዮጵያን ማየት ነው

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ፍቅር ያሸንፋል

ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)