በቴክኖሎጂ ዘርፍ ለጀመረችው ተፈላጊ ሥራ የአራት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያገኘችው ኢትዮጵያዊት

ዮዲት የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ የጀመረችው ገና በ14 ዓመቷ ነው። “ከሁሉም በፊት ቴክኖሎጂስት ነኝ። በሕይወት ዘመኔ በቴክኖሎጂ ዙሪያ ብዙ ሥራዎችን የሠራሁ ቢሆንም እንኳን አብዛኛውን ጊዜ የኮምፒውተር ፕሮግራም በመገንባት ነው ላለፉት 2 ዓመታት የኖርኩት” የምትለው ዮዲት የተወለደችው በዩናይትድ ኪንግደም ነው።

ዮዲት ስታንተን

BBC Amharic : አባቷ ለኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ድርጀት ይሠሩ ስለነበር ዮዲት ከቤተስቧ ጋር ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በመዘዋወር ነው ያደገችው።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በመወለዷና በተለያዩ አገራት እየተዘዋወረች በማደጓ “አብዛኛውን ጊዜ በጭንቅላቴ ውስጥ ነው የምኖረው፤ ምክንያቱም መርከብ ላይ ጊዜ እንዲሁ በቀላሉ አያልፍም። ለማሳለፍ ደግሞ ብዙ የጭንቅላት ሥራን ይጠይቅ ነበር” ትላለች።

ወደ ፕሮግራሚንግ ዓለም ስትቀላቀል በእርሷ ዕድሜ የነበሩት ልጆች ሃሳብ ወደ ጨዋታ ያዘነብል የነበረ ቢሆንም፣ ዮዲት ግን የመጀምሪያው ላፕቶፕ ኮምፒውተሯን አስተማሪዋ እንደ ስጦታ ካበረከተላት ጊዜ አንስቶ ቴክኖሎጂ ዓለሟ ሆነ።

የአስተማሪዋ ለጋሽ መንፈስ እዚህ፣ ማለትም ዛሬ ለደረሰችበት ቦታ እንዳበቃት ምስክርነት የምትሰጠው ዮዲት፣ ያንን ውለታ ዘወትር ታስታውሳለች።

ዮዲት ወደ አሜሪካ ሚሺገን ለትምህርት ተልካ በነበረበት ወቅት፣ ካርል የሚባል የሁለተኛ ደረጃ አስተማሪዋ ለኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ያላትን ፍቅር በማየት ካገለገሉ ዕቃዎች መደብር የመጀመሪያ ላፕቶፕ ኮምፒውተሯን ገዝቶ እንዳበረከተላት ትናገራለች።

ዮዲት ነዋሪነቷት በዩናይትድ ኪንግደም ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ባሕር እና ውቅያኖስ ላይ ስታሳልፍ፣ መሬት ስትረግጥ ደግሞ በኢትዮጵያና በሌሎች አገራት መካከል ነው ያደገችው።

የ’ኦፕን ሴንሰርስ’ መስራች የሆነችው ዮዲት “ከፕሮግራሚንጉ ባሻገር፣ እናትም ነኝ” ትላለች።

“ውብ እና ጎበዝ ሁለት ሴት ልጆች አሉኝ። በተለይ በኮቪድ ወቅት ሥራዬንም እነርሱም ከቤት ሆኖ ማስተዳደር ለየት ያለና አስቤው የማላውቀው ተሞክሮ ነው የሆነኝ” ብላለች።

ዮዲትን የዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂ ድርጅት መስራችና አስተዳዳሪ መሆኗ የሚደነቅላት ቢሆንም እንኳን ለየት የሚያደርጋት ግን በተሰማራችበት የሥራ ዘርፍ ብዙም ሴቶች በተለይ ከአፍሪካ የመጡና ጥቁር ሴት ቴክኖሎጂስቶች አለመኖራቸው ነው።

ሴቶች በጣት የሚቆጠሩበት ኢንዱስትሪ

በዮዲት አንደበት በዚህ ዘርፍ ክፍተቱ የሴቶች በበቂ ሁኔታ አለመኖር ሳይሆን፣ በሥራው ከፍ ያለ የአለቅነት ወይም ኃላፊነት ደረጃ ላይ የደረሱ ሴቶች አለመኖራቸው ነው።

ይህንንም ስታስረዳ “አብዛኛውን ጊዜ ሥራውን ስለማይችሉት ወይም ስለሌሉ ሳይሆን፣ ዕይታው እነርሱ ላይ ባለመሆኑና የዕድገት ዕድሎች ብዙም ስለማይከፈቱላቸው ነው” ብላለች።

አክላም “በሕይወቴ ሴት ስለሆንኩኝ አልችልም የሚል ስሜት ተፈጥሮብኝ አያውቅም። ዕድለኛ ሆኜም የነበርኩበት ትምህርት ቤትም ትችላላችሁ በሚል ስሜት ያሳደገን ሲሆን የሚያበረታታ እንጂ የሚያደናቅፍ አልነበረም” በማለት የአራት ሚልየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍን ተቀባይ ብቸኛዋ ጥቁር ኢትዮጵያዊት ሴት ለመሆን ያበቃት ይህ እንደሆነ ትገልጻለች።

ቀጥላም “ልክ እንደማንኛውም የሥራ ዘርፍ ‘ሲስተሙ’ ችግር ስላለበትና ከዚያም በተጨማሪ ደግሞ የምንሠራው ሥራ ለማራመድ ገንዘብ ይጠይቃል፣ ገንዘቡም ለኢንዱስትሪው ከተመደበው የድጋፍ ገንዘብ ላይ ነው ለድርጅቶቹ በፈንድ/ድጋፍ መልክ የሚሰጠው፤ እናም ከተመደበው ገንዘብ አብዛኛውን ጊዜ 0.02 በመቶው ብቻ ነው በጥቁር ሴት የተመሰረቱ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች የሚያገኙት” ስትል ታስረዳለች።

“ገና ስጀምር በወንድ ስምና ፎቶግራፍ ነበር በተለያዩ የፕሮግራሚንግ መድረኮች ላይ እሳተፍ የነበረው፣ እናም ብዙዎች ለረዥም ጊዜ ወንድ እመስላቸው ነበር። እኔ ማንነቴን እንዳያውቁ ነበር ይህን ያደረግኩት፤ ማለትም ከደኅንነት አንፃር” የምትለው ዮዲት በቴክኖሎጂ ዓለም አብዛኛው ሰው ‘ሱዶኒም’ ወይም የሐሰት ስም እንደሚጠቀሙ ትጠቅሳለች።

“ሴቶችን አትችሉም ማለት እንደ ኃጢያት መቆጠር አለበት” የምትለው ዮዲት፣ “አትችሉም ሲባል ማንም ሰው ያለመቻል ስሜት ይፈጠርበታል፤ ደግሞም የአእምሮን ሰላምና ጤናም ጭምር ይነሳል። ስለዚህ ትችላላችሁ በማለት ሰውን ማበረታት አስፈላጊ ነው” ትላለች።

ዮዲት ለተለያዩ ድርጅቶች የሠራች ሲሆን፣ የእራሷን ድርጅት እንድታቋቁም የገፋፋት እናት መሆኗ እንደሆነ ትናገራለች። በዚህም ‘ኦፕን ሴንሰርስ’ የተሰኘውን ድርጅት የመሰረተችው እ.አ.አ. በ2013 ነበር።

ለሌሎች የቴክኖሎጂ ድርጅቶች አማካሪ ሆና በምትሠራበት ወቅት እንደ ጊዜ ማሳለፊያ ከጎን ያዝ አድርጋው እንደነበር የምትገልጸው ዮዲት አሁን ግን ሥራው ዋና መተዳደሪያዋ ነው ትላለች።

ዮዲት ስታንተን

የፎቶው ባለመብት, Yodit

ኦፕን ሴንሰርስ እንዴት ተጀመረ?

ልጇ ድክ ድክ በምትልበት ጊዜ በጣም ኃይለኛ አስም ይዟት ለመተንፈስ በተቸገረችበት ወቅት መፍትሄ ይሆናል የምትለውን ነገር ስታወጣና ስታወርድ ነበር የድርጅቷ ሐሳብ የተጠነሰሰው።

እንዴት? ስትባልም፣ ዮዲት በወቅቱ የአየሩን ሁኔታ የሚለካ ሶፍትዌር ፕሮግራም በመሥራት በሰፈሯ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ትገጥማቸዋለች።

ከዚያም የልጇ አስም የሚነሳበትን ጊዜና በዚያኑ ሰዓት ላይ ያለውን የአየር ሁኔታ በማጥናት ምን አይነት ነገሮች የልጇን አስም እንደሚቀሰቅስባት ለማወቅ ቻለች።

ይህን ጥናት፣ ዮዲት ታካሄድ የነበረው በትርፍ ጊዜዋና ከሥራ ሰዓት ውጪ ቢሆንም የምታገኛቸውን ውጤት በበይነ መረብ በማሳተም በዓለም የተለያዩ ክፍሎች ያሉ ሰዎች በሥራዋ ውሰዕጥ ይሳተፉ እንደጀመር ትናገራለች።

ከእነርሱም መካከል ከጃፓን፣ ከአሜሪካ እና ከሌሎችም አገራት የአየር ሁኔታ መረጃ በማሰባሰብ ጥናታቸውን እያካሄዱ በነበረበት ወቅት አንድ ባለሃብት የመሥሪያ ቤቱን የአየር ሁኔታ የማሻሻል ፍላጎት እንዳለው እና ጉዳዩን አጥንታ መፍትሔ እንድታቀርብለት አማከራት።

በዚህ የተጀመረው ሥራ የኦፕን ሴንሰርስ ደንበኞችን እያበዛ መጥቶ አሁን የድርጅቷ የሙሉ ጊዜ አስተዳዳሪ ሆና እየሠራች ትገኛለች።

ዮዲት ያመረተቻቸው መሳሪያዎች

የፎቶው ባለመብት, Yodit

ዮዲት ያመረተቻቸው መሳሪያዎች

ዮዲት እንዴት የአራትሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኘች?

ዮዲት በቴክኖሎጂ ዘርፍ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ፈታኝ መሆኑን ስታስረዳ ኢንዱስትሪው በነጭ ወጣት ወንዶች መሞላቱን ታነሳለች።

በመሆኑም ከተፎካካሪዎቿ የሚጠበቀውና ከአንዲት ጥቁር ኢትዮጵያዊት ሴት የሚጠበቀው ማስረጃ እኩል አለመሆኑን ትገልጻለች።

“ስለዚህ እኛም [ጥቁር ሴቶች] ደግሞ የድጋፉ ገንዘብ በ0.02 በመቶ ብቻ ወደእኛ ሊመጣ እንደሚችል እያወቅን ሥራችንንም ማሰረጃችንንም ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስተን ማጠንከር እንዳለብን እናውቃለን። እሱኑ ነው የምናደርገው” ስትል ታክላለች።

በመቀጠል “…የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታችን የሥራችንን ጥራት የሚያስመሰክር በመሆኑ ትልቅ ደስታ እንዲፈጠርልን ከማድረጉ ባሻገር ሌሎች ደንበኞችን የምናገኝበትና ሥራችንን የምናስቀጥልበትም ስም ጥለን እያለፍን ነው” በማለት ታስረዳለች።

በአሁን ጊዜ የሥራ ወይም የሥራና አካባቢዎች ሁኔታ እየተቀየረ እየመጣ በመሆኑ አሠሪዎች ወይም ድርጅቶች አብረው መቀየር እንዳለባቸው ትመክራለች።

“በተለይ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በሥራ ቦታዎች ያለውን አየር የመቆጣጠሩና የማጥናቱ ሥራ በይበልጥ አስፈላጊ እየሆነ ነው። ዋናው ዓላማችን ሰው በሚሰበሰብበት በማንኛውም ሥፍራ ያለው አየር ንፁህና ጤናማ እንደሆነ ማጣራት ነው” ስትል ሥራዋን ትገልጻለች።

የዮዲት ሥራ የዓለማችን የወቅቱ ሁኔታ የሚፈልገው መፍትሄ መሆኑን የተገነዘቡት ክሬን ቬንቸር ፓርትነርስ የተባሉ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ሥራዋን እንድታስፋፋ አራት ሚሊዮን ዶላር በመስጠት አብረዋት እየሰሩ ነው።

ዮዲት ለዓመታት የገነባችው ተቋሟ አሁን በዓለም ዙሪያ የመታወቅና የመፈለግ ዕድልን እያገኘ ነው በዚህም የሥራ ውጤቷ በዩናይት ኪንግደም፣ በአውሮፓ አገራት ውስጥና በሰሜን አሜሪካ ተፈላጊነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።

ከዚህ ባሻገር ዮዲት ሥራዋን ወደፊት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ የማስፋፋት ዓላማ አላት።