ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሆሮ ጉድሩ ወለጋ በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ ናቸው

በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን፤ አሙሩ ወረዳ የሚገኙ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሚደርስባቸው ”ዛቻና ማስፈራሪያ” ወፌ እና ኢላሞ ከሚባሉ የገጠር ከተሞች ተሰደው በአጋምሳ ከተማ በሚገኝ ት/ቤት ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸውልናል።

በቁጥር 11 ሺ ይሆናሉ የተባሉት ነዋሪዎች ወደ አማራ ክልል በመሰደድ ላይ እያሉ ተከልክለው በትምህርት ቤቱ መጠለላቸውን ችግራቸውን ለማስረዳት ወደ አዲስ አበባ ሰላም ሚኒስቴር የመጡት ሼህ ሀሰን መሐመድ ይናገራሉ።

ከእነዚህ ከተሞች በተጨማሪ በብዙ ሺ የሚቆጠር ህዝብ በገጠር እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ጉዳዩን ለማስረዳት ወደ አዲስ አበባ የመጡት አራት ሆነው እንደሆነ የሚገልጸው ካሳነው አህመድ ከአከባቢው 40 አባወራ አስቀድመው መውጣታቸውንና አሁን ላይ በዛህ ለሚገኙ ወገኖቻቸው ለማመልከት እንደመጡ ይናገራል።

”አሁን ላይ ህይወታቸውን በእንዴት እንደሚያመልጡና እንደሚያተርፉ ለማመልከት ነው የመጣነው” ሲል በጹሑፍ ለሰላም ሚኒስቴር ማስገባታቸው፤ ሆኖም የሚያናግራቸው እንዳላገኙ ይናገራል።

በወረዳው የኦነግ ሸኔ ኃይል በምን ደረጃ ይገኛል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም ”አከባቢው ላይ ወዲያ ወዲህ ሲል የሚታየው ሸኔ ነው መሳሪያ እናከፋፍላለን እስከማለትም ደርሰዋል” ሲል ምላሹን ያስቀምጣል።

አክሎም ድርጊቱን በመቃወም ከእኛ ጎን የነበሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ከአስር በላይ ተገድለዋል ሲል ይናገራል።

በአጋምሳ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት እንደተጠለለ የሚናገረውና ስሙ ለጊዜው እንዲጠቀስ ያልፈለገ ግለሰብ የተወሰነ መኪና ወደ ጎጃም መውጣቱንና ነዋሪዎቹ ተበታትነው እንደሚገኙ ገልጾ አሁን ላይ 3800 የሚሆኑት ብቻ መኖራቸውን አንስቷል።

ሐምሌ ወር ከገባ ጀምሮ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ሐምሌ1፣ ሐምሌ 4ና ሐምሌ 16 ጥቃት የተፈጸመባቸው ቀናት ናቸው ሲሉ ያነሱ ሲሆን አሁን ላይ ምን ያህል ሰው እንደሞተ ማስቀመጥ ባይቻልም ከሃያ የሚልቁ ሰዎች በዞኑ ባሉ ወረዳዎች ሞተዋል ነው የተባለው።

የኢሰመጉ ሐምሌ 15 ቀን ባወጣው መግለጫ በኡሙሩ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ በሕግ ቁጥጥር ስር የነበሩ ከ250 እስከ 300 የሚደርሱ ሰዎች ሐምሌ 11፤ 2013 ከግምጃ ቤት መሳሪያ እና ጥይት መዝረፋቸውንና እነዚሁ ሰዎች በዕለቱ ከሌሊቱ ስድስት እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ሲተኩሱ ማደራቸውን የሚጠቁም መረጃ እንደደረሰው ገልጿል።

አክሎም “በወረዳው ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች ከአካባቢው መውጣት አትችሉም ተብለው በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን አቤቱታ አቅርበዋል” ሲልም የሁኔታውን አሳሳቢነት አስገንዝቧል።

ምንጭ ቲክቫህ ኢትዮጵያ