የመከላከያ ሠራዊት ለቆ ከወጣ በኋላ የመስፋፋት ምልክቶችን ያሳየው የትግራይ ክልል ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሔ ይገኝለት ይሆን?

ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የመከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል የተሰጠውን ተልዕኮ አቋርጦ እንዲወጣ መንግሥታቸው ሲወስን መሠረት ያደረጋቸውን ምክንያቶች ገልጸው ነበር።

ከዘረዘሯቸው ምክንያቶች ትልቁን ድርሻ የያዘው ከትግራይ ክልል ቀውስ ጀርባ በክልሉ ያለው ውጊያ እንዲቀጥል የሚያፋፍሙ የውጭ እጆች መኖራቸው ነው።  በቀጥታ በስም የማይጠቅሷቸውን የእጆቹ ባለቤቶች ‹‹ሐዋሳ ያሉ ሰዎች›› በማለት በምሳሌ የጠቀሷቸው ሲሆን፣ እነዚህ ‹‹ሐዋሳ ያሉ ሰዎች›› በአንድ በኩል መንግሥት ዘንድ ቀርበው በትግራይ ክልል የሚወስደው የሕግ ማስከበር ዕርምጃ ትክክል እንደሆነ፣ እነሱም ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሟቸው በተመሳሳይ መንገድ እንደፈቱት ያስረዳሉ ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ትግራይ ክልል ከሚገኙት ጋር ተገናኝተው በመንግሥት በኩል የተያዘውን አቋም በመረጃ መልክ ያቀርባሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እነዚህ የሐዋሳ ሰዎች ከፋፍለው ያጫውቱን እንጂ ከእነሱ (ትግራይ ካሉት) ጋር ተገናኝተው ይመክራሉ፤›› ብለዋል።

ይህንን ሁኔታ በማጤን በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያንና የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ ጥልቅ ፖለቲካዊ ትንተናና ምክክር ተደርጎ፣ ሠራዊቱ ከትግራይ ክልል እንዲወጣ ከመወሰኑ በፊት መካሄዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስረድተዋል።

በዚህ የፖለቲካ ትንተና ከተወሰዱ ተሞክሮዎች አንዱ 30 ዓመታት የፈጀው የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኤርትራ ነፃነነቷን ከማግኘቷ አስቀድሞ ከኢትዮጵያ ጋር ለ30 ዓመታት ስትዋጋ ከሁለቱም ወገኖች ጀርባ ጦርነቱን የሚያፋፍሙ የውጭ እጆች እንደነበሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለ30 ዓመታት ሲዋጉ የጦርነቱ ትጥቅና በጀት በሙሉ የእነሱ እንዳልነበረና ሊሆንም እንማይችል በመግለጽ፣ ‹‹ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ጀርባ ሆነው አስፈላጊውን ቅመም እየጨመሩ በደንብ ያባሉን የውጭ ኃይሎች ነበሩ። የፈለጉትም የደቀቀች ኢትዮጵያና የደቀቀች ኤርትራን መፍጠር ነበር፣ ያገኙትም ይህንን ነው፤›› ብለዋል።

አሁን ያለውን የትግራይ ክልል ግጭት በተመለከተም ጦርነቱ እንዲቆም የሚፈልግ ብዙ ኃይል አለመኖሩን መንግሥታቸው እንደገመገመ ገልጸዋል።

‹‹እንዲሁ እየተዋጋን፣ እየተጋጋጥን የደቀቀች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር እየገፉን ነው፡፡ ይህንን የሚያሳዩ አደገኛ ልምምዶችም ዓይተናል፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

‹‹በመሆኑም ይህንን አደገኛ ልምምድ ወጣ ባለ መንገድ ማየት እንጂ፣ በተቀደደልን ቦይ መፍሰስ የለብንም ብለን፣ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ተሞክሮ ውጪ ተመሳሳይ ሁነቶችን ያለፉና የሚታይባቸው አገሮችን ተሞክሮ በመተንተን ከትግራይ ለመውጣት ወስነናል፤›› ብለዋል።

የውሳኔው ማጠንጠኛ የነበረውን በአንድ ምሳሌ ሲገልጹትም፣ ‹‹ለዶሮ በሽታ በሬ ማረድ ትክክል አይደለም የሚለው የአገራችን አባባል አግጦ መጣ። ስለዚህ ተገደን ነው የገባነው፣ በፈለግነው ሰዓት ጦርነቱን አቁመን መውጣት ያስፈልጋል ብለን ወጣን። ይህ የጥሞና ጊዜ ለእኛም ለሌላኛው ወገንም ያስተምራል ብለን እናስባለን፤›› ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ለፌዴራል መንግሥት ባቀረበው ደብዳቤ መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም እንዲያደርግ ጠይቆ እንደነበር፣ ይህንን ጥያቄም የፌዴራል መንግሥት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ተቀብሎ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ለሕዝብ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ከትግራይ ክልል ለቆ የመውጣት ውሳኔው ከወር በፊት እንደተወሰነ፣ ሠራዊቱን የማውጣት ሥራም ከአንድ ወር በፊት በሚስጥር ሲካሄድ ቆይቶ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. መታወቁን ገልጸዋል።

ሠራዊቱን የማስወጣት ተግባር ሳይነገር የተካሄደበት ምክንያትም ወታደራዊ ሚስጥር በመሆኑ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የመንግሥታቸው ውሳኔ የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ ሲገልጹም፣ ‹‹ውሳኔያችን ትክክል ነው ብለን እናምናለን። ለዶሮዋ ብለን በሬውን አናበላሽም። ውጤቱ ምን እንደሚሆን ደግሞ በጋራ የምናየው ይሆናል፤›› ነበር ያሉት።

ከተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔው በኋላ የተስተዋለው የቀውሱ መስፋፋት

የመከላከያ ሠራዊት ለቆ ከወጣ በኋላ የመስፋፋት ምልክቶችን ያሳየው የትግራይ ክልል ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሔ ይገኝለት ይሆን?የፌዴራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን ተከትሎ፣ የሕወሓት ኃይል የተለቀቁትን የትግራይ ከተሞች በሙሉ ከተቆጣጠረ በኋላ ወታደራዊ እንቅስቃሴውን ወደ ምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች አድርጓል።

እነዚህ አካባቢዎች ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በትግራይ ክልል የአስተዳደር ወሰን ውስጥ የቆዩ ቢሆንም፣ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ያካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በአካባቢዎቹ ላይ የማንነትና ታሪካዊ የባለቤትነት ጥያቄ ሲያነሳ በነበረው የአማራ ክልል ቁጥጥር ሥር ወድቀዋል።

የአማራ ክልል በአካባቢዎቹ የራሱን አስተዳር መሥርቶም ላለፉት ሰባት ወራት አካባቢዎቹን እያስተዳደረ እንደቆየ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የፌዴራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ማወጁንና ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን ተከትሎ ግን፣ የሕወሓት ኃይል እነዚህን አካቢዎች ለመቆጣጠር ጊዜ ያልወሰደ የትጥቅ ትግል ማካሄድን ዕርምጃው በማድረግ እስከ ማይፀብሪ ድረስ መቆጣጠር የቻለ ሲሆን፣ በመቀጠልም በራያ በኩል መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በማካሄድ እስከ አላማጣና ኮረም፣ እንዲሁም ደግሞ ከሰሞኑ ወደ ቆቦ የተጠጋ ጥቃት ማካሄድ ጀምሯል።

ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስና በአካባቢዎቹ ላይ ታሪካዊ የባለቤትነት መብት የሚያነሳው የአማራ ክልል የሕወሓትን እንቅስቃሴ ለመቀልበስና ባለቤትነቱን ለማፅናት፣ ‹‹የህልውና ዘመቻ›› የተሰኘ የክተት ጥሪ ለክልሉ ሕዝብ በማቅረቡ በሁለቱ ክልሎች ወሰን ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ ፍጥጫና በየዕለቱም መጠነኛ ውጊያ ይደረጋል።

ከዚህ ባለፈም ዘጠኝ ክልሎች በሥራቸው ከሚገኙ የልዩ ኃይሎች አባላትን ቀንሰው፣ ሕወሓት በአማራ ክልል በኩል የደቀነውን አዲስ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ በአሁኑ ወቅት አሰማርተው ይገኛሉ።

የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ከመውጣቱ አስቀድሞ ከተለያዩ አካላት ጋር ሚስጥራዊ ውይይት ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የገለጹ ሲሆን፣ በተለያየ ደረጃ በተካሄደው በዚህ ውይይት ተሳታፊ ከነበሩ አካላት መካከል አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ ምሁር፣ ይህ ሁኔታ እንደሚከሰት እሳቸው በተሳተፉበት ውይይት ተነስቶ እንደነበር ለሪፖርተር ገልጸዋል።

የተኩስ ማቆም ውሳኔው ተገቢ የመሆኑን ያህል፣ ውሳኔውን ተከትሎ የሕወሓት ኃይል በክልሉ የምዕራብ አካባቢዎች የሚኖረውን ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጡ ሥነ ሥርዓቶች መሠረት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ፍላጎት እንደማያሳይ፣ በዚህም ምክንያት የተኩስ አቁሙ ተጨናግፎ ወደ ጦርነት የመመለሱ ጉዳይ ተነስቶ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ነገር ግን በአማራ ክልል ልሂቃን በኩልም አካባቢዎቹ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱና ክልሉ በአካባቢዎቹ ላይ ያለውን ጥያቄ አቆይቶ ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ ከተሰጠ በኋላ በሕግ አግባብ እንዲመለሱ ለማድረግ ፍላጎት ባለመታየቱ፣ ሌሎች አማራጮችን ለማየት ተሞክሮ እንደነበር ያስረዳሉ።

በአማራጭነት ከተነሱት ውስጥም ሁለቱም ወገኖች ጥያቄ በሚነሱባቸው አካባቢዎች ላይ ሕግን መሠረት ያደረገ መፍትሔ እስኪመጣ ድረስ፣ አካባቢዎቹ ከሌሎች ክልሎች በሚወጣ ገለልተኛ አካል እንዲተዳደሩ የሚል ሐሳብ ቀርቦ እንደነበርና ተቀባይነት እንዳላገኘ ይጠቁማሉ።

ሁሉም በኃይል መፍትሔ ለማግኘት የሚፈልግ በመሆኑም አሁን ወዳለው ሁኔታ እንደተገባ፣ አሁን ነገሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዴት እንደሚቻል ማወቅ አስቸጋሪ ነው ይላሉ።

የሕወሓት ኃይል አካባቢዎቹን በትጥቅ ትግል መልሶ ለመያዝ ለሚያደርገው ሙከራ የአማራ ክልል ኃይል መልሶ በመምታት እየተከላከለ ሲሆን፣ የመከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች ክልሎች የተወጣጣው ኃይልም ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተሰማርቶ የማጥቃት ዕርምጃ እንዲወስዱ ከመንግሥት ትዕዛዝ እየጠበቁ መሆኑን የመከላከያ ሠራዊቱ ሰሞኑን አስታውቋል።

መንግሥት የማጥቃት ዕርምጃ የሚወስን ውጊያው በአንድ ዕዝ ሆኖ፣ በመከላከያ ሠራዊቱ የሚመራ እንደሚሆንም ከመከላከያ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በአማራ ክልል ያለው ውጥረት ነግሦ ባለበት በዚህ ወቅት የሕወሓት ኃይል የፌዴራል መንግሥት ያልጠበቀውን ጦርነት በአፋር ክልል በኩል ከሐምሌ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍቷል።

ከአላማጣ አዋሳኝ በሆነችው ያሎ ወረዳ ወደ አፋር ክልል ጥቃት በመሰንዘር ወረዳዋን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው የሕወሓት ኃይል በቀጣዮቹ ቀናት ከያሎ አካባቢ ወደ ውስጥ 37 ኪሎ ሜትር ድረስ እንደዘለቀ፣ በአሁኑ ወቅትም አውራና ሲፍራ በተባለች የአፋር ከተማ እየተዋጋ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

የሕወሓት ኃይል በአፋር በኩል ጥቃት የከፈተው አፋርን እንደ ጠላት ቆጥሮ ሳይሆን፣ የፌዴራል መንግሥትን ለማዳከም መሆኑን አስታውቋል።

የአፋር ክልል ሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ሻለቃ ኢብራሂም ሁሙድ በበኩላቸው፣ የሕወሓት ኃይል በአፋር ክልል ያደረገው ድንገተኛ ጥቃት ፖለቲካዊ ዓላማን ያነገበ እንደሆነ ይገልጻሉ።

እሳቸው እንደሚሉት የሕወሓት ኃይል በአፋር በኩል ጥቃት በመክፈትና እስከ ሚሌ ድረስ በመዝለቅ፣ የአገሪቱ የወደብ ኮሪደር የሆነውን የአዲስ አበባ ጂቡቲ መንገድ ለመቆጣጠር የሚያደርገው ሙከራ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ የአፋር ልዩ ኃይል የሕወሓትን ጥቃት እየመከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

እስካሁን ባደረገው ጥቃትም በርካታ የሰው ሕይወትና ሰብዓዊ ቀውስ በአፋር ክልል መከሰቱን ገልጸዋል።

የአፋር ክልል የአደጋ መከላከልና የምግብ ደኅንነት ኮሚሽነር አቶ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው፣ የሕወሓት ኃይል በከፈተው ጥቃት ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ ከ54 ሺሕ በላይ የአፋር ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል። ይህንን የሕወሓት እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከሰሞኑ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ‹‹ጁንታ›› ብለው የሚጠሩት የሕወሓት ኃይል ቆም ብሎ እንዲያስብና ተኩስ አቁሞ ወደሚፈልገው የፖለቲካ ድርድር እንዲገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ከትግራይ ለቆ የወጣው በመንግሥት የፖለቲካ ውሳኔ ላይ ደርሶ በማዘዙ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሕወሓት ኃይልን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመስማት ከፍተኛ ፖለቲካዊ ጫና በመንግሥትና በሠራዊቱ ላይ መፍጠሩን የገለጹት ጄኔራሉ፣ ከዚህ ባለፈም መንግሥት ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ተገንዝቦ ባሳለፈው ውሳኔ ሠራዊቱ ከክልሉ ለቆ መውጣቱን አስረድተዋል።

በየትኛውም አገር ያሸነፈ ኃይል የተናጠል ተኩስ አቁም እንደማያውጅ የገለጹት፣ ጄነራል ብርሃኑ የመንግሥት ውሳኔ፣ ‹‹ዋጋ ያስከፈለ ቢሆንም››፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ኃላፊነት ከሚሰማው መንግሥት የመጣ ውሳኔ መሆኑን አመልክተዋል።

‹‹ጁንታው ቆም ብሎ እንዲያስብና ተኩስ አቁሞ የፖለቲካ ጥያቄ ካለው እንዲደራደር እንመክራለን። በቅድመ ሁኔታ የተሽቆጠቆጠ የፖለቲካ ድርድር ሰላም አያመጣም። እንደምንሰማው ዓይነት ፉከራ የሚቀጥልና ሁሉንም በጉልበትና በኃይል ለማድረግ የሚፈልግ ከሆነ አይቻልም። ትዕዛዝ ብቻ ነው የምንጠብቀው። ዕርምጃ ለመውሰድ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ ነን፤›› ብለዋል።

የሕወሓት ኃይል በአፋር በኩል ውጊያ ከመክፈቱ ባለፈ፣ በክልሉ የተጠለሉ የኤርትራ ስደተኞች ከክልሉ ውጪ እንዳይወጡ ማድረጉን መንግሥት የገለጸ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይህንን ድርጊት በዝምታ እንዳለፈው በመጥቀስ ወቀሳውን ሰንዝሯል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል እስከ 7,000 የሚሆኑ የኤርትራ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ሕወሓት በበኩሉ በዓለም አቀፍ የስደተኞች አያያዝ ሕግ እንደሚገዛ በመግለጽ ኤርትራዊያኑ ያለ ፍላጎታቸው ወደ ሌላ አካባቢ ሊዘዋወሩ እንደማይችሉ አስታውቋል።

መንግሥት የኤርትራ ስደተኞችን ከግጭት ቀጣና ለማውጣትና በጎንደር አካባቢ በተከፈተ ካምፕ ለማስፈር ለዓለም አቀፍ ተቋማት ያደረገው ጥሪ ጆሮ አለማግኘቱን የገለጸው የስደተኞችና የስደት ተመላሾች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ፣ የኤርትራ ስደተኞች በአሁኑ ወቅት ዕገታ የሚመስል ሁነታ ውስጥ መውደቃቸውን ገልጿል።

በሌላ በኩል ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በትግራይ ክልል የሚገኙ የፌዴራል መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ያቀኑ ተማሪዎች፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ከክልሉ መውጣቱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ ባለመቻላቸው ሥጋት ላይ ወድቀዋል።

ቤተሰቦቻቸውም ዓርብ ሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጽሕፈት ቤት በመገኘት መፍትሔ የጠየቁ ሲሆን፣ የሕወሓት ኃይል ተማሪዎቹ እንዳይወጡ ከልከላ አለማድረጉን ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በትግራይ ክልል የተቋረጡ የስልክና የባንክ አገልግሎቶችን የፌዴራል መንግሥት ባለመልቀቁ፣ ተማሪዎቹ ለመውጣትና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት እንዳልቻሉ በመጥቀስ የዕገታ ሁኔታ ውስጥ ሳይከታቸው እንዳልቀረ ሥጋት ፈጥሯል።

በሌላ በኩል የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በአሁኑ ወቅት ጦርነት ውስጥ የሚገኙትን የሕወሓት አመራሮች ጨምሮ፣ በአጠቃላይ በ62 የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ ባለፈው ዓርብ መሥርቷል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የትግራይ ክልል ቀውስ ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ መፍትሔው ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ የገባ ቢሆንም፣ የአሜሪካ መንግሥት ከወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ከሆኑት የዴሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዚዳንትና ከኬንያ ፕሬዚዳንት ጋር ለትግራይ ክልል ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈለግ መምከሩ ታውቋል።