በአፋር የምናደርገው ዘመቻ በጣም ውስን እና ከኦሮሚያ ክልል የመጡ የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ ኃይሎች ላይ ያነጣጠረ ነው – ጌታቸው ረዳ

የትግራይ አማጽያን ቃል አቃባይ ጌታቸው ረዳ በአፋር ክልል የሚያደርጉት ዘመቻ በጣም ውስን እና ከኦሮሚያ ክልል የመጡ የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ ኃይሎች ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል። ነገር ግን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የትግራይ አማጽያን አፋርን ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ሊነጥል ወረራ መፈጸማቸውን ተከትሎ ይህንኑ ለመከላከል ሲባል የኦሮሚያ ኃይሎችን መጋበዛቸውን ተናግረዋል። እናም አፋር «ጁንታው» ያሉትን ኃይል ለማስቆም በአንድነት ሊቆም ይገባል ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። በአፋር ክልል እየተደረገ ያለው ጦርነት ከስምንት ወራት በላይ በትግራይ ክልል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ወደ አጎራባች ክልሎች እየተስፋፋ ስለመምጣቱ ማሳያ ነው ሲል የፈረንሳይ የዜና ምንጭ ዘግቧል።

የአፋር ክልል መስተዳድር ከትግራይ አማጽያን ተከፈተብኝ ላለው ጥቃት የክልሉ ሕዝብ ተጥቅ አንግቦ ራሱን እንዲከላከል ጥሪ ማቅረቡ ተዘገበ። ጥሪውን ተከትሎ በክልሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ከመኖርያቸው ያፈናቀለው የሰሞኑ ውግያ ወደ ለየለት ጦርነት እንዳያመራ አስግቷል።የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በክልሉ ብዙኃን መገናኛ ቀርበው ማንኛውም አፋር ባለው የጦር መሳርያ ምድሩን ያስጠብቅ ዘንድ ጥሪ ማቅረባቸውን ዘገባው አክሏል። የትግራይ አማጽያን ባለፈው ሳምንት የመንግስት ደጋፊ ወታደሮችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት በአጎራባቹ የአፋር ክልል መክፈታቸውን አስታውቀው ነበር። በጥቃቱ ከ20 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ ከ70,000 የሚልቁት ደግሞ ከመኖርያቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል።