ወልቃይት/ራያን ከመከላከል ባለፈ ጦርነት መደረግ የለበትም #ግርማክሳ

[addtoany]
አንዳንድ ወገኖች የፌዴራል መንግስት ተኩስ አቁሙን እንዲቀለብስ ሲጠይቁ ይሰማሉ፡፡ አንዱም እኔው ነበርኩ፡፡ ምክንያቱም ወያኔ ዘልቃ ራያና ጠለምት በወራራ ስለገባኝ፡፡አሁን  የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሺያዎች በሚያኮራ መልኩ ከአንድ ቀን በላይ ሳትቆይ ወያኔን ከራያና ጠለምት አስወግደዋታለ፡፡ከዚህ በኋላ ዳግም ወያኔ ስትመጣ ለመቅጣት መዘጋጅት እንጂ በትግራይ ዘልቆ በመግባት ጦርነት መደረግ ያለበት አይመስለኝም፡፡
ሕወሃት መደምሰስ አለበት ? አዎን በሚገባ፡፡ አሁን አይደለም ፣ ሕወሃት ለብቻው አፈንግጦ የራሱን እንቅስቃሴ ማድረግ ሲጀምር፣ ከሁለት አመት በፊት፣  “ሕወሃት መደምሰስ አለበት። አሸባሪ ቡድን ተደርጋ መበየን አለበት” ብዬ ብዙ ጊዜ ጽፊያለሁ፡፡ ሕወሃት ለትግራይ ሕዝብ ነቀርሳ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሽታ ለአካባቢውም ደግሞ እርግማ የሆነው ቡድን ነው፡፡ መደመሰስ ያለበት ቡድን።
አንዳንድ ወገኖች ሕወሃት መደምሰስ አለበት ስንል ጦርነት ብቻ የሚመስላቸው አሉ፡፡ አይደለም፡፡ እንደውም ከዚህ በኋላ ከመከላከል ውጭ ጦርነት መደረግ አለበት ብዬ አላምንም፡፡ ያለ ጦርነት ሕወሃትን መደምሰስ ይቻላል።
  1. ሙሉ ለሙሉ የህወሃትን ወታደራዊ አቅም ዜሮ ማስገባት፣
  2. የሕወሃትን የኢኮኖሚ አቅም መግደል፣
  3. የሕወሃትን አስተሳሰብና አይዲዮሎጂዎች ፣ የፖለቲካ መርህዎች ተቀባይነት እንዳይኖራቸውና እንዲሸነፉ ማድረግ፣
  4. የሕወሃትን የአለም አቀፍ ድጋፍ እንዲቁረጥ ማድረግ፣
  5. የሕወሃት ማህበረሰባዊ ድጋፏን እንድታጣ መስራት፣
  6. የሕወሃት መዋቅር መበታተንና ዳግም የፖለቲካ ኃይል ሆና እንዳትመለስ ተደርጋ ፖለቲካዊ አቋሙን መምታት
ማለት ነው፡፡
የሕወሃት ኢኮኖሚ አቅም
የሕወሃት የኢኮኖሚ አቅሟ መዳከም ብቻ ሳይሆን መሉ ለሙሉ ዜሮ ሊገባ የቀረው ትንሽ ነበር፡፡ ሆኖም ግን አሁን በትግራይ እያስተዳደሩ ያሉት ሕወሃቶች ስለሆኑ፣ ለሕዝብ ተብሎ የሚሰበሰበውን እርዳታ በአሻጥር እየወሰዱ ሰራዊቶቻቸውን የመቀለብ አቅም መልሰው ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
እንደዚያም ሆኖም ግን ብዙ ገፍቶ መሄድ አይቻልም፡፡ ሕዝቡ ፉርኖ ዱቄት ሰልፍ ተሰለፎ እየለመነ ረዘም ላለ ጊዜ ሊኖር አይችልም፡፡
የሕወሃት ወታደራዊ አቅም
የሕወሃት ወታደራዊ አቅም ያንን ያህል የገፋ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሆኖም ግን በእርዳታ ስም በርካታ መሳሪያዎችን የማስገባት እድል አላቸው፡፡ የእርዳታ ጭነቶች በሚገባ እየተፈተሹ ካልገቡ፡፡
መከላከያ ከትግራይ ለቆ ሲወጣም ብዙ መሳሪያ እጃቸው ገብቷል፡፡ እነ ዶር አብይ አህመድ ፣ “መሳሪያዎችን ትተን ነው የወጣነው” ያሉት ውሸት እንደነበረ መቼም የማያውቅ ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡
እንደዚያም ሆኖ ግን ከአንድ አመት በፊት የነበራቸው ወታደራዊ አቅም አንድ አስረኛ እንኳን አሁን አላቸው ብዬ አላምንም፡፡ የሕወሃት አቅም ያንን ያህል አስፈሪ ነው ማለት አይቻልም፡፡
የአብይ አህመድ አገዛዝ በአሻጥር መከላከያ ከራያ እንዲወጣ መወሰኑን ተከትሎ ወያኔዎች ሮጠው ራያን፣ ማይጠምሪ አካባቢ ተቆጣጥረው ነበር፡፡ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሺያዎች በአንድ ቀን ነው ጠራረገው ከራያና ከማይጠምሪ ያስወገዷቸው፡፡ የወያኔ ሚሊታሪ አቅም ምን ደረጃ እንዳለም የራያውና የማይጠምሪው ዉጊያ ፍንትው አድርጎ ነው ያሳየን፡፡ የወልቃይትማ ጉድ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ተከዜ ተሽግረው መጥተው ወያኔዎች እንደ ቅጠል ነው የረገፉት፡፡
የሕወሃት ማህበረሰባዊ ድጋፍና አቅም
ሕወሃት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሁለት የማህበረሰባችን ክፍሎች ድጋፍ አለው፡፡ አንደኛው ከሕወሃት የጥቅም ተጋሪ ከነበሩ፣ ጥቅማቸው ስለተነካባቸው ካኮረፉ ፣ ወይንም ደግሞ “ሕወሃት ከሌለች የኛም አቅም ይዳከማል” ከሚሉ የብሄር ብሄረሰብ ተወካዮች ፣ በዋናነት ደግሞ ከኦሮሞ ብሄረተኛ ፖለቲከኞች ነው፡፡ እነዚህ በጣም ብዙ አይደሉም፡፡ ግን በጣም በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እየሰሩ አብዛኛው ሕዝብ በሕወሃት ፕሮፖጋንዳ እንዲሳሳት በማድረግ ዙሪያ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ያሉ ናቸው። በተለይም በዉጭ ያሉ።
ሌሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የትግራይ ማህበረሰብ አባላት ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል ሕወሃትን የማይደግፉ፣ ግን በትግራይ ዉጊያ በነበረው ሁኔታ፣ በዚያም በተሰራው ግፍ የተበሳጩ፣ “የአብይ መንግስትና የኢሳያስ መንግስት ሊያጠፉን ነው የመጡት” በሚል ፊታቸውን፣ ባይፈልጉም ወደ ሕወሃት ያዞሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶችም እንደ ቀድሞ ኢትዮሜዲያ ኤዲተር አብርሃ በላይ፣ ህወሃትን ይቃወሙ የነበሩ፣  ህወሃትን ወደ መደገፍ የዞሩም አሉ፡፡
እነዚህን የሕወሃት ማህበረሰባዊ የድጋፍ መሰረቶች ላይ ካልተሰራ፣ ሕወሃትን መደምሰስ አይቻልም፡፡ ሕወሃት ሚሊዮን ወይ መቶ ሺሆች ደጋፊ እስካለው ድረስ ሕወሃትን የሚደገፉት ከሕወሃት እንዲነጠሉ ማድረግ የትግሉ፣ ሕወሃትን የመደምሰስ፣  ትልቁ ስትራቲጂ መሆን አለበት፡፡
የሕወሃት አለም አቀፍ ድጋፍና አቅም
ትልቁና በቀላሉ መመከት ያልተቻለው የሕወሃትን የአለም አቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ አቅም ነው፡፡ ይሄም በዋናነት ከሕወሃት በተጻራሪ የቆመው ሌላ ኢትዮጵያዊ በመከፋፈሉ፣ የመንግስትን አቋም እንዲያንጸባርቁ የተመደቡ ዲፕሎማቶች እጅግ በጣም ደካማ በመሆናቸውና በዋናነት የአብይ መንግስት ራሱ በሚሰራቸው በርካታ ስህተቶች ምክንያት ነው፡፡ ዶር አብይ ብዙ ጊዜ የዉጭ አገራት ልኡካንን  የዋሸበት ሁኔታ እንደነበረና አገራችን በዉጭ ዲፕሎማቶች ዘንድ እንድትናቅ የተደረገችበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
የአብይ መንግስት ፣ በትግራይ ያለውን ቀውስ ተዉት፣ በተቀረው ኢትዮጵያዉያን መካከል መግባባት፣ አንድነት ፣ የበለጠ ትስስር እንዳይኖር ያደረገ፣ ሕወሃትን ተክቶ በተረኝነት መንፈስ እየጋለበ ያለ አገዛዝ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደውም ከሕወሃት የባሰ ነው ለምን እደግፋለሁ የሚሉም አሉ፡፡ እነ አጣዬ፣ ሻሸመኔ፣ መተከል፣ አርሲ፣ አዳይቱ  ወዘተ ያሉ ኢትዮጵያዉያን ቢጠየቁ፣ ማን ይሻላችሁ  ነበር ተብለው ቢጠየቁ ምን  ሊመልሱ እንድሚችሉ መገመት አያቅትም።
የሕወሃት የአስተሳሰብና የፖለቲካ አይዲዮሎጂ አቅም
ሕወሃትን ሕወሃት የሚያሰኘው ድርጅቱና አባላቱ ብቻ አይደለም፡፡ የድርጅቱ የፖለቲካ አስተሳሰቦችም እንጂ፡፡ እነዚህ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ካልተሸነፉ፣ ሕወሃት ማሸነፍ ወይንም መደምሰስ አይቻልም፡፡
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን የፌዴራል መንግስት የሚቆጣጠረው በዶር አብይ የሚመራው የበዳዲና/ኦህዴድ አገዛዝ ፣ ሙሉ ለሙሉ የሕወሃትን ኮተት ሕገ መንግስትና የጎሳ አወቃቀር ለማስቀጠል እየተጋ ያለ፣ ከሕወሃት በተወሰነ መልኩ የባሰ ዘረኛ አገዛዝ ነው፡፡ በሌላ አባባል ሕወሃት በኦህዴድ ውስጥ በመንፈስ እየኖረ ነው፡፡
ይህ አስተሳሰብ እስከቀጠለ ድረስ ሕወሃት አይደመሰስም። በመፈስን መኖሩ ይቀጥላል፡፡
ማጠቃለያ
ሕወሃት በኢኮኖሚና በውትድርና ያለው አቅም በማዳከሙ ዙሪያ ብዙ ተጨማሪ ነገር ማድረግ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፤ የሚመጡ እርዳታዎች ከመፈተሽ ውጭ፡፡ ወልቃይት ጠገዴ፣ ራያ ፣ ጠለምት ሕወሃት ዘልቃ እንዳትገባ አስፈላጌውን ዝግጅትና ጥንቃቄ ከማድረግ ባለፈ፣  ሌላ ወታደራዊ እርምጃዎች መወሰድ የሚያስፈልግ አይመስለኝም።
የሕወሃትን አስተሳሰብና ፖለቲካ ለማሸነፍ ፣ እንቅፋት የሆነው ኦህዴድ በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ አስገዳጅ እንቅስቃሴዎች በማድረግ የዘር ፖለቲካ እንዲታገድ፣ የዘር ህገ መግስትና አወቃቀር እንዲለውጥ ከመቼም ጊዜ በላይ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው፡፡
የወያኔን የአለም አቀፍ ግንኙነት የማህበረሰባዊ መሰረት ድጋፍ እንዲቀንስ ብሎም እንዲጠፋ ለማድረግ፣
  • በተቀረው ኢትዮጵያ ባሉ የትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ፕሮፋይሊንግ ማስቆም ብቻ ሳይሆን የማንታገስ መሆን መቻል አለብን
  • ለትግራይ ሕዝብ የሚያስፈልገው ድግፍ (ተፈትሾ) ወደ ትግራይ እንዲገባ የተቀላጠፈ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ለእርዳታ ስራ የሚያሳፈልጉ መሰረታዊ የስልክ፣ የመብራት የዉህ አገልግሎቶች እንዲደርሱ መደረግ አለበት፡፡
  • በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መንግስት ሰራሽ የፖለቲካ ቀውሶች የሚፈቱበትን፣ በቅንነት ላይ ያተኮረ ብሄራዊ ውይይት መጀመር አለበት፡፡ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት አለባቸው፡፡ ተደረገ የተባለው ምርጫ የጨረባ ምርጫ መሆኑን በመረዳት፣  ሁሉን አቀፍ ጊዚያዊ መንግስት መቋቋም አለበት፡፡ ኢትዮጵያዉያን አንድ እንድንሆን፡፡ ያኔ እነ አሜሪካ አርፈው ይቀመጣሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ዶር አብይ አህመድ ከስልጣኑ እንዲነሳ ቢደረግ ለኢትዮጵያ አዲስ ጉልበት አዲስ ጅማሪ (fresh start ) ሊሆንም ይችላልና ቢታሰብበት ጥሩ ነው።
  • ትግራይን ተሻግሮ ሌላ ጦርነት መደረግ የለበትም፡፡ ራሱ የትግራይ ሕዝብ ወያኔን አሽቀንጥሮ እንዲጥል እድል ሊሰጠው ይገባል፡፡ በመሆኑም ወያኔን እንዲታገልልን የምንፈልገውን ሕዝብ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ጦርነት ከተደረገ ሕዝቡን ያዳክማል፡፡ ወያኔዎችን ደግሞ ኃይል ያገኛሉ፡፡ ከዚህ በፊት የተሰራውን ስህተት መልሶ መድገም አያስፈለግም፡፡
  • የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ ኤምባሲዎች፣ የመንግስት ኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤቶች እንደገና ከታች ወደ ላይ ተዋቅረው በባለሞያዎች መሞላት አለባችው፡፡ ይሄ ምድረ ካድሬ ሁሉ መነሳት አለበት፡፡
  • ሕወሃት በትግራይ የምትፈጽማችውን ወንጀሎች በየጊዜው እየተከታተሉ ማጋለጥ ፣ የአለም ማህበረሰብ እንዲያውቀው መደረግ አለበት፡፡ ይሄንን ለማድረግ፣ ተሳዳቢ ካድሬዎችን ሳይሆን፣ ተግተው የሚሰሩ፣ ማሳመን የሚችሉ፣ ጨዋነት የተላበሱ፣ አጭበርባሪ ያልሆኑ አክቲቪስቶችን ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡