በማሰቃያነት ሲያገለግል የነበረው የጅግጅጋ ማዕከላዊ እስር ቤት ተዘጋ ፡፡

የሱማሌ ክልል በማሰቃያነት ሲያገለግል ነበር ያለውን የጅግጅጋ ማዕከላዊ እስር ቤት በይፋ ዘጋ

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚገኘውና በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ንጹሀን ዜጎች የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይፈጸምበት ነበር የተባለውን ኦጋዴን ተብሎ የሚጠራው ማእከላዊ ማረሚያ ቤት በዛሬው እለት ተዘጋ ፡፡

የሶማሌ ክልል መንግስት በአሁኑ ጊዜ ትኩረት ሰጥቶ እየወሰደ ከሚገኘው የለውጥ እርምጃዎች መካከል ባለፉት አመታት በክልሉ ህዝብ ላይ ሲፈጸሙ የነበሩትን የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ ዋነኛው ነው፡፡

የክልሉ መንግስት ካቢኔ ከትላንት ወዲያ ባካሄደው ስብሰባ በክልሉ ባለፉት አመታት በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ንጹሀን ዜጎች የሚታጎሩበትና በህዝቡ ላይ ከፍተኛ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸምበት የነበረ ነው በሚል በጅግጅጋ ከተማ የሚገኘውን ማእከላዊ ማረሚያ ቤት እንዲዘጋ ወስኗል፡፡

በዚህ መሰረት በዛሬው እለት በክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ የሚመራ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ፤ ታዋቂ ግለሰቦች ፤ ሙሁራን እንዲሁም ለረጅም አመታት በተለያዩ የአለም ክፍሎች በመዟዟር በክልሉ የሚፈጸሙትን የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶችን ሲቃወሙና ሲታገሉ የቆዩት አክቲቪስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ አብዱላሂ ሁሴንና አክቪስቲስት አብዱረሺድ አሊ ሸአ በተገኙበት ማረሚያ ቤቱ በዛሬው እለት በይፋ ተዘግቷል፡፡

በዛሬው እለት የተዘጋው የጅግጅጋ ከተማ ማእከላዊ ማረሚያ ቤት የሚገኙ እስረኞች ህጉን መሰረት በማድረግ እንደሚለቀቁም ከክሉ መንግስት ለኢቢሲ የተላከው መግለጫ ያለክታል፡፡

የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባርም በትዊተር ገፁ እንዳስታወቀው የማሰቃያ ማዕከሉን መንግስት ለመዝጋት መወሰኑ መልካም እርምጃ ሲል በትዊተር ገፁ አወድሶታል፡፡