ለሰላም ከሃዘናችን ጋር ተንበርክከናል!! (አሌክስ አብርሃም)

ለሰላም ከሃዘናችን ጋር ተንበርክከናል!!
(አሌክስ አብርሃም)

ጋሞዎች ናቸው ! ወንድ ሴት ሳይል በባህላቸው መሰረት ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዙሪያ በግፍ ለተጨፈጨፉ ልጆቻቸው በእንብርክክ እየሄዱ ሃዘናቸውን ሲገልጹ የሚያሳይ አሳዛኝ ምስል ነው!! ፌስቡክ ላይ መጻፍ ከጀመርኩ ጀምሮ በጣም ብዙ አሳዛኝ ምስሎች አይቻለሁ ፣ ወገኖቻችን ሊቢያ በርሃ ላይ የታረዱበትን ቪዲዮም ተመልክቻለሁ! ያኔ እልህ በቀል እና መጠቃት ነበር ውስጤን የሞላው! ይሄንኛው ግን ምሬት ነው የሞላኝ ! ሃዘንና ጠባቂ የለሽነት ነው የተሰማኝ! አያችሁ እነዚህ ሰዎች ጋሞዎች ናቸው ታሪካቸውን ብትመለከቱ የስራ ሰዎች ፣ ሲጠቁ ደግሞ እንኳን ባልቴትና ህጻን ጨፍጫፊ የመንደር ዱርየ እኔነኝ ያለ ብርቱ የማያስቆማቸው ጦረኞች!! ግን ለደረሰባቸው ግፍ ሰይፍ መዘው አልወጡም፣ ወንድሞቻቸው ላይ ጦር አልሰበቁም! ተንበርክከው ፍትህ ነው የለመኑት ! አንጀት የሚያንሰፈስፍ ጨዋነት የፕሮፖጋንዳ ሳይሆን ህያው የሆነ ትሁትነታቸውን ነው ያሳዩት! ከልጅ እስካዋቂ ብርቱ ጉልበቶቻቸው በሃዘን ተንበርክከዋል!!

ዛሬም ለነዚህ መንግስት አለን ህዝብ አለን ብለው በተቀመጡበት በግፍ ለተጨፈጨፉ ትሁት የጋሞ ወንድሞቻችን እንዲሁም ሌሎችም ሚስኪን ኢትዮጲያዊያን የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ መንግስት ሃቀኛ ፍትህ እንዲሰጥ በየሚዲያው ወንጀለኞችን ለመሸፈን የሚደረገውን ግብ ግብ እና አይን ያወጣ አሳዛኝ ሃላፊነት የማይሰማው ፕሮፖጋንዳ ያስቆም ዘንድ ሁላችንም ተንበርክከን እንጠይቃለን!! ለፍትህ እንበረከካለን!!