DW : በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደረገው ምርጫ በአሶሳ ዞን የተወዳደረው የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ቤ.ህ.ኔ.ን) በዞኑ ምርጫ በተሟላ መልኩ በሶስት ወረዳዎች ውስጥ የተካሄደው ምርጫ ፍትሃዊ እና ተአማኒነት አልነበረውም ሲል ቅሬታውን ለምርጫ ቦርድ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሐመድ ኢስማኤል የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በአባሎቻቸው እና ተወካዎቻቸው ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ማሳደራቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡
በምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ለማ ምርጫው ህጉን ጠብቆ አልተካሄደም የሚሉና የመንግስት አመራሮች ምርጫ አስፈጻሚ ሆነው ተስተውሏል ተብለው በቤ.ህ.ኔ.ን ፓርቲ በኩል የቀረቡት ቅሬታዎች ስህተት ናቸው ብለዋል።
የምርጫ አስፋጻሚዎች ከማንኛውም ፓርቲ ገለልተኛ ሆነው ቦርዱ አምኖባቸው የመደባቸው ናቸው ብለዋል፡፡ ።ማንኛውም ፓርቲ ቅሬታ ማቅብ እንደሚችልና በህጉ አግባብ ምላሽ እንሚሰጥም አክለዋል፡፡
የቤኒሻንል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካሚል ሀሚድ በበኩላቸው ምርጫ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በሙሉ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዎች እና ታዛቢዎች በተገኙበት ሰላማዊ በሆነ መልኩ መካሄዱን ገልጸው የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ቤ.ህ.ነ.ን) ያቀረበው ክስ የሀሰት ክስ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዩጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅሬታ በቀረበበት የአሶሳ ዞን ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች ባጋጠመው የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እንዲቋረጥ አድርጓል። DW