የተቃውሞው ጎራ አንዱ ባንዱ ሲስቅ ጀንበር ጥልቅ እንደሚባለው ከመሆን አልዳንም – ተክሌ በቀለ ከኢዜማ

ተክሌ በቀለ ከኢዜማ – የተቃውሞው ጎራ ብንደማመጥ ፣ ብንመካከር ፣ ብንከባበር ፣ ብንተባበር የጎላ አስተዋፅኦ እናደርግ ነበር ። የሂደት እና የግዜ ጉዳይ ቢሆንም ምናልባት ወድቀንም እንነሳለን ። አንዱ ባንዱ ሲስቅ ጀንበር ጥልቅ እንደሚባለው ከመሆን አልዳንም ። ከስህተት ተምረን እንጠነክራለን ብየ ተስፋ አደርጋለሁ ።
የፈለግነውን ስም እንስጠው በዚህ ምርጫ ችግሩን ሁሉ ተጋፍጣችሁ ለአዜማውያን ድምፅ የሰጣችሁን አምናችሁን ነው ።እናመሰግናለን! ያልመረጣችሁን ልታርሙን ነው ። እናመሰግናለን !!
ይህ እንዳለ ሆኖ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የአዲስ አበባው ድምፅ ግን አሁን ያለውን በቋንቋ ላይ መሰረቱን ላኖረው የፌደራል ስርአት የማስቀጠያ ህዝበ ውሳኔ አይደለም ። የጋራ አንድነታዊ እሳቤን ለማጎልበት ቢሆን ከህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት በላይ የሚያስተሳስረው ዜግነታዊ ወንድማማችነት ይሆን ነበር ።
ከዚያ ይልቅ ካለፉት ስህተቶች ተምሮ የጋራ እሳቤን ለማጎልበት ቅንነት ለጎደለው ፣ በራስ ፍቅር ለወደቀው እና ቁመናውን ላላስተካከለው የተቃውሞ ጎራ የማስተማሪያ ውሳኔ ነው ፣ የተቃውሞ ጎራው የመከፋፈል ውጤት ነው ። የሃገራዊ አንድነትን አደጋ የገመገመ የህልውና ማስቀጠያ የጭንቀት ድምፅም ነው ።
በግሌ እንደ ዜጋ ፣ አባልና የህ/ተ/ም ተወዳዳሪ ለኢዜማ በመሰላችሁ መንገድ ለለፋችሁ ያላችሁን ሁሉ ሳትሰስቱ ለሰጣችሁ ጓዶች በሙሉ ከፍ ያለ ክብር አለኝ ። ኢዜማችን የሆነ ግዜ የሆነ ቦታ ላይ የሳተው መንገድ እንዳለ ደግሞ ይሰማኛል ። ይህን በውስጥ ማየት ይቻላል ።
ለኢዜማ በአጠቃላይ እንዲሁም በኢዜማ አደረጃጀት መሰረት በግል የምርጫ ወረዳየ ላይ በጉልበታችሁ ፣ በእውቀት እንዲሁም በገንዘብም በሞራልም ላገዛችሁኝ ለደከማችሁልኝ ሁሉ ለሃገራችን ዲሞክራሲ የከፈላችሁት ዋጋ ቢሆንም ከፍ ያለ ልባዊ ምስጋናየ ይድረሳችሁ ። እንደ ወደድኩ እንዳከበርኳችሁ እኖራለሁ ።
ሰላም እና ፍቅር ለሁላችን!! ተክሌ በቀለ ከኢዜማ