የቴሌኮም ጥቅል አገልግሎቶችን በህገ-ወጥ መንገድ ለደንበኞች በመሸጥ ላይ የተሳተፈ የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኛ በህግ ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኛ በህግ ቁጥጥር ስር ዋለ

የቴሌኮም ጥቅል አገልግሎቶችን በህገ-ወጥ መንገድ ለደንበኞች በመሸጥ ላይ የተሳተፈ የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኛ በህግ ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

ሰራተኛው ኩባንያው ያወጣውን የሲስተም አጠቃቀም ፍቃድ ፖሊሲ እና የቴሌኮም ማጭበርበርን ለመከላከል የወጣውን ፖሊሲ በመጣስ ከ3ሺ በላይ ጥቅል አገልግሎቶችን ለ2 ሺ 1 መቶ 35 ደንበኞች በህገ-ወጥ መንገድ በመሸጥ ሲሳተፍ እንደነበር ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

በኩባንያው የደህንነት ቡድን ክትትል ሲደረግበት የነበረው ሰራተኛው ህገ-ወጡን ተግባር ሲፈፅም እጅ ከፍንጅ ተይዞ ለህግ አስከባሪ አካላት ተላልፎ መሰጠቱም ተገልጿል፡፡

ከህገ ወጥ ተግባሩ ጋር በተያያዘ ተገቢውን ክፍያ ሳይፈጽሙ ግልጋሎቱን ሲያገኙ የነበሩ የ2 ሺ 135 ደንበኞች አገልግሎት መቋረጡንም ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

በመሰል ህገ-ወጥ ተግባራት በሚሳተፉ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ የሚያደርገውን ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም ተግባሩን በማጣራት አግልግሎትን እስከማቋረጥና በህግ ተጠያቂ እስከማድረግ የደረሰ እርምጃን እንደሚወስድ ይፋ አድርጓል፡፡

ህዝቡ የቴሌኮም ማጭበርበር ተግባራት በሀገር ደህንነትና ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሱትን አደጋ በመገንዘብ ለጸጥታና ለህግ አስከባሪ ተቋማት ጥቆማውን በማቅረብ ህገወጦችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ኢትዮ ቴሌኮም ጥሪ አቅርቧል።