የኮሚሽነር አበረ አዳሙ የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ተፈጽሟል፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞው ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ሥርዓተ ቀብር በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል። በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ቤተሰቦቻቸው፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መገኘታቸውን የአሚኮ መረጃ ያመለክታል።

የኮሚሽነር አበረ አዳሙ አጭር የህይወት ታሪክ

May be an image of 2 people, people standing and military uniformኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከአባታቸው ከአቶ አዳሙ መኮንን እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጦቢያ ንጋቱ የካቲት 13 ቀን 1961 ዓ.ም በቀድሞው የጎጃም ክፍለ ሀገር፣ ቆላ ደጋ ዳሞት አውራጅ፣ደጋዳሞት ወረዳ፣ መለስ ብሳና ሜዳ ቀበሌ ተወለዱ።

ኮሚሽነር አበረ አዳሙእንደማንኛውም የአካባቢው ተወላጅ እድሜያቸው ለትምህርት እስኪደርስ በቤተሰቦቻቸው እንክብካቤ አድገው በ1973 ዓ.ም ወይን ውኃ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው እስከ 8ኛ ክፍል ተማሩ፡፡የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ሀገር አቀፉን የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ 9ኛ ክፍል ተዛወሩ።ተወልደው ባደጉበት አካባቢ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቅርብ ባለመኖሩ ከትውልድ አካባቢያቸው ርቀው መሄድ ስለነበረባቸው አጎታቸው ይኖሩበት ወደ ነበረበት አምቦ ከተማ በመሄድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በላቀ ውጤት አጠናቀዋል።ወደ አዲሰ አበባ በመምጣት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ባወጣው የመኮንነት ፈተና ተሳትፈው በማለፋቸው በፖሊስ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ የሚሰጠውን የመኮንነት ትምህርት አጠናቀው በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ በፖሊስ ዲፕሎማ በ1986 ዓ.ም ተመረቁ፡፡


ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ከተመረቁ በኋላ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዞን 2፣ ወረዳ 21፣ ቂርቆስ ፖሊስ ጣቢያ ተመድበው በወንጀል መከላከል፣ ወንጀል ምርመራና በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለአምስት ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ በኃላፊነት በነበሩበትም ሰዓት ወንጀልን በመከላከል፣ ህዝብን በማገልገል ተደጋጋሚ ሽልማት ያገኙ ሲሆን በወቅቱ በነበረው ስርዓት መመሪያን አይቀበልም በሚል ተራ ሰበብ ከሦስት ጊዜ በላይ በመሪዎች ለእስር ተዳርገው ነበር። ኮሚሽነር አበረ ይህንን በደል በመጠየፍ በቀድሞው የደህንነት ኃላፊዎች የተደገሰላቸውን ሞት በማምለጥ ከሀገራቸው ለመሰደድ ተገደዋል።


May be an image of 3 people and outdoorsኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከአያቶቻቸው በወረሱት ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ህወሓት መራሹን መንግስት በኃይል ለመጣል ወደ ኤርትራ በረሀ በመውረድ “የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር” የሚባል ድርጅት ከትግል ጓደኞቻቸው ጋር በመመስረት የወታደራዊ ክንፍ አዛዥ በመሆን ሲታገሉ ቆይተዋል። ከዚያም ትግሉን ለማስፋትና ህወሓት መራሹን መንግሥት ከሥልጣን በፍጥነት ለማውረድ ከኤርትራ በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን፣ በኬኒያና በዩጋንዳ ትግሉን ሲመሩ ቆይተዋል።


በኋላም እራሳችውን ከቀጥታ የትግል ተሳትፎ ለተወሰነ ጊዜ በማግለል በኬንያ ሊሙሩ ከተማ በሚገኘው የአሜሪካን ዩኒቨርስቲ የነፃ ትምህርት ዕድል በማግኘታቸው በሊደርሽፕ ማኔጅመንት ዲግሪያቸውን የሰሩ ሲሆን የአራት ዓመቱን ትምህርት በ2 ዓመት በላቀ ውጤት አጠናቀዋል። በዓለም አቀፍ ስደቶኞችና ሰብዓዊነት ረጅ ተቋማት አማካኝነት ወደ ስዊድን ሀገር በማቅናት በስደተኝነት ይኖሩ ነበር። ከዚያም “ግንቦት ሰባት የነፃነትና የእኩልነት ንቅናቄን” ከመስራች አባልነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ አመራርነት በመምራት ታግለው አታግለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በስዊድን ሀገር የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል።


በስዊድን ቆይታችውም ከታዋቂው የሉንድስ ዩኒቨርስቲ (Lunds University) ሕግና የማህበረሰብ ሳይንስ ጥናት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (MSC in Sociology of Law) በከፍተኛ ውጤት ያገኙ ሲሆን የመመረቂያ የምርምር ጽሁፋቸው በዩንቨርስቲው ተመርጦ ታትሟል፡፡መጽሀፋቸውም በአሁኑ ወቅት በታላቁ የበይነ-መረብ መገበያያ በሆነው በአማዞን በሽያጭ ላይ ይገኛል። ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከሌላኛው በስዊድን ሀገር አንጋፋና ታዋቂ ከሆነው ማልሞ ዩኒቨርስቲ (Malmo University) ሌላኛውን ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ስደተኞችና የማህበረሰብ ግንኙነት (MA in International Migration and Ethnic Relations) በከፍተኛ ማዕረግ አግኝተዋል፡፡


May be an image of one or more people, people standing, military uniform and outdoorsኮሚሽነር አበረ በስዊድን ሀገር እያሉ ተጨማሪ የመጀመሪያ ዲግሪ በሕግና በፖሊስ ሳይንስ (BA in Legal and Police Science) ከሌላኛው የስዊድን ታዋቂ ከሆነው ሊኔኖስ ዩንቨርሲቲ (Linnaeus University) አግኝተዋል፡፡ ከእነዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህታቸውን ጨርሰው፤ ጥሩ ገቢ የሚያሰገኝ ሥራ አግኝተው፤ ልጆች ወልደው፤ ከትግሉ ጎን ለጎን የግል ኑሯቸውን ማጣጣም ጀምረው ነበር፡፡ በሀገራችን አንፃራዊ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ በተደረገላቸው ጥሪ ህዝባቸውን ለማገልገል ወደ ሀገራቸው ገብተዋል። በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን ታሪክ የመጀመሪያው በፖሊስ ሳይንስ የተመረቀ ፖሊስ ኮሚሽነር በመሆን ከየካቲት 2011 ዓ.ም እሰከ ሚያዝያ 2013 ዓ.ም ድረስ በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡


ኮሚሽነር አበረ ስለ ሀገራቸው ተናግረው የማይጠግቡ፤ ለህዝባችው ልዩ ፍቅር ያላቸው፤ ሁሉም ነገር ከሀገር እና ከህዝብ በታች ነው ብለው የሚያምኑ፤ሀገራቸውን እና ህዝባቸው እንዳስቀደሙ የኖሩ እውነተኛና ሀቀኛ አርበኛ ነበሩ። ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ቆፍጣና ወታደር፣ ምሁር፣ ደራሲ፣ ገጣሚ እና የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ ከሦስት በላይ ቋንቋዎችን ማለትም (አማርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ኦሮምኛ) አቀላጥፈው መናገርና መፃፍ የሚችሉ በሁሉም ዘርፍ በሚባል ደረጃ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነበሩ።
ኮሚሽነር አበረ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሪፎርም ጥናት በማድረግና በመምራት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድጋቸውም በላይ ሪፎሩሙን በቁርጠኝነት በመምራት አመርቂ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ያደረጉ ነበሩ፡፡


በአጠቃላይ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባላቸው ጥልቅ የሀገርና የህዝብ ፍቅር ስሜት የተነሳ የራሳቸውን ቤተሰብ መስዋዕት በማድረግ ከተመቻቸ የውጭ ሀገር ኑሮ ህዝቤን አገለግላለሁ በሚል ከለውጡ ዋዜማ ጀምረው በወኔና በፍፁም የሀገር ፍቅር ስሜት ወደ ሀገር ቤት መጥተው በአልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የአማራ ብሔራዊ ክልልን ከፀጥታ ቀውስ የታደጉ፤ በሠራዊቱ አመራሮችና አባላት ዘንድ እጅግ በጣም ተቀባይነት የነበራቸው፤ አስተዋይ፣ ቅንና ተግባቢ ነበሩ፡፡ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ሙያዊ ብቃትና ክህሎት የነበራቸው፤ ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ-ምግባር የተላበሱ ባለምጡቅ አዕምሮ ነበሩ፡፡


ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ልዩ ኃይሉን፣ የመደበኛ ሠራዊቱንና በተቋሙ ሥር ያሉትን ሠራተኞች የሚመዝኗቸው በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በዕውቀታቸው፣ በሥነ-ምግባራቸውና በሥራ ብቃታቸው እንጂ በሌሎች መመዘኛዎች አይደለም፡፡ ኮሚሽነሩ አምርረው የሚጠሉ ብቻ ሳይሆኑ አድሏዊ አሰራርንና ኢ-ፍትሐዊነትን በመቃወም ነፍጥ አንስተው በረሃ የወረዱና በሚችሉት ሁሉ የታገሉ ጀግና መሪ ነበሩ፡፡


ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ህወሓት የአማራ ክልልን በእብሪት በወረረችበትና ኢትዮጵያን በእናት ጡት ነካሽነት በወጋችበት ጊዜ ቁርጠኛ አመራር የሰጡና የአማራ ልዩ ኃይልና ሚኒሻ በሕግ ማስከበሩ ሂደት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያስመዘገበውን ዘመን ተሻጋሪ ገድል ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ተጠቅመው በመምራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ነበሩ፡፡


ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች አባት የነበሩ ሲሆን ሚያዚያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ድንገት ባጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም ሆስፒታል ገብተው በህክምና ላይ እያሉ በተወለዱ በ52 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የክልሉ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖችና የፖሊስ አባላት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊወርጊስ ካቴዴራል ቤተክርስቲያን ሚያዚያ 28 ቀን 2013 ዓ/ም ተፈጽሟል፡፡