ከሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት የሚፈጥር እና የሚተባበር ማንኛውም አካል በህግ ተጠያቂ ይሆናል – ጠቅላይ አቃቢ ህግ

(ዋልታ) – 5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 6ኛ አመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባው ከዚህ ቀደም በሚኒስትሮች ምክር ቤት “ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ” (ህወሃት) እና “ሸኔ” በሽብረተኝነት እንዲሰየሙ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዚህም ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት የሚፈጥር እና የሚተባበር ማንኛውም አካል በህግ ተጠያቂ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
በአሸባሪነት የመሰየም ዋነኛ አላማው በህብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን የሽብር ተግባር ለማስቆም እና ለህግ አስከባሪ አካላትም ወንጀሉን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር መሆኑ ተመላክቷል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት “ህወሃት” እና “ሸኔ” በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲፈጽሙት ከነበረው የሽብር ተግባር እና የንጹሃን ሞት አንጻር የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ የዘገየ ቢሆንም ተገቢ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ “ህወሃት” እና “ሸኔ” በንጹሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንዲፈጸም ምክንያት የሆኑ ቡድኖች በመሆናቸው ውሳኔ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ አካላት ለሀገር እድገት ጸር እና ለዜጎች ሰላም እንቅፋት ሲሆኑ የቆዩ በመሆናቸው በአሸባሪነት መፈረጃቸው በሀገር ውስጥ የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል እና የህዝብን ደህንነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ አንድ ድርጅት በሽብርተኝነት ከተሰየመ ንብረቶቹ እንዲወረሱ እና የፋይናንስ አቅሙን ለማዳከምም እድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡ በሽብርተኝነት መፈረጃቸው ሊኖራቸው የሚችለውን የሰው ሃይል ተሳትፎም ለመቀነስ ያስችላል ነው የተባለው፡፡ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳቡን መርምሮ “ህወሃት” እና “ሸኔ”ን በአንድ ድምጸ ታዕቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ ነው ውሳኔው ያስተላለፈው፡፡