የመንግስት ተቀደሚ ስራው የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ መሆን አለበት – ሰላም ፍለጋ ቤታቸውን ጥለው የሸሹ

“…የመንግስት ተቀደሚ ስራው የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ መሆን አለበት” – ሰላም ፍለጋ ቤታቸውን ጥለው የሸሹ የቲክቫህ አባላት

የፅሁፍ መልዕክት ያስቀመጡ የቲክቫህ አባላት የመንግስት ተቀዳሚ ስራው የዜጎችን ደህንነት እና ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሰላም እና ደህንነት በሌለበት እንዴ መኖር ይችላል ? እንዴት ነው ሀገር አለኝ ብሎ ሰርቶ ፣ ለፍቶ ፣ ቤተሰብ መስርቶ የወደፊት ተስፋን ሰንቆ መኖር የሚቻለው ? ሲሉ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ እጅግ ሰፊ ሀገር ናት የሚሉት የሰላም እጦት ገፈጥ ቀማሽ ነን ያሉ አባላቶቻችን ፦
– በተደጋጋሚ ሰላም የሚናጋበት ፣
– ፀጥታ የሚደፈርስበት ፣
– ዜጎች በግፍ የሚገደሉበት ፣
– ዜጎች፣ ንብረታቸውና ቤታቸው የሚወድምበት አካባቢዎች ይታወቃሉ ፤ የስጋት ቀጠናዎች በደንብ ይለያሉ በነዚህ አካባቢዎች ችግሮች ሳይፈጠሩ መከላከል ይገባል ፤ ችግሮች ከተፈጠሩ በኃላ እንዳይሰፋና ጥፋተኞች ተለይተው ሌላው እንዳይደግመው አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።

ችግር አለባቸው በሚባሉባቸው ቦታዎች ቀድሞ በቂ የፀጥታ ኃይል በመመደብ ፣ ቀድሞ በመዘጋጀት ፣ ከምንም በላይ ደግሞ አንድም ሳይቀር ጥፋተኛን በመያዝ ለፍርድ ማቅረብ እንደሚገባ ገልፀዋል።

መንግስትም እራሱ ውስጡን ፈትሾ በተደጋጋሚ ጊዜ ችግር በሚፈጠርባቸው ቦታዎች ተሳትፎ ያላቸውን አካላት መለየት ይኖርበታል ፤ ተቀዳሚ ስራው የህዝብ ደህንነት ማስጠበቅ ነው ብለዋል።

ስርዓትና ህግ የሌለበት ሀገር እስኪመስል ከተሞች ሲወድሙ ፣ ዜጎች ሲገደሉ ፣ ቤቶች ሲቃጠሉ ፣ ድርጊት ፈፃሚዎችን መቆጣጠር ሳይቻል ቀርቶ የለየለት ስርዓት አልበኝነት ነግሶ ማየት ለነገ የሀገሪቱ ህልውና እጅግ አደገኛ ምልክት ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።