ሩሲያ ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማድረግ ሀሳብ አቅርባ በተደራዳሪ ሀገራት መልስ አልተሰጣትም ተባለ

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በግብፅ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ዛሬ ሰኞ ከግብፁ አቻቸው ሳሚ ሹክሪ ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫው ወቅት ፣ ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በግብፅ ፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል “የሁሉም ወገኖች ጥቅም የሚረጋገጥበት ስምምነት መደረስ አለበት” ብለዋል፡፡

ሩሲያ በድርድሩ ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማድረግ ሀሳብ አቅርባ እንደነበር ያስታወሱት ሚስተር ላቭሮቭ ፣ ይሁንና በተደራዳሪ ሀገራት መልስ እንዳልተሰጣት ነው ያነሱት፡፡

“የአፍሪካ ሕብረት የሕዳሴ ግድብን ችግር መፍታት አለበት” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪ በበኩላቸው “በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በመተማመን ላይ ነን” ብለዋል፡፡

ከግድቡ ጋር ያለውን አለመግባባት ሩሲያ መገንዘቧን የገለጹት ሚኒስትሩ ፣ ሩሲያ በግድቡ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ወሳኝ ሚና መጫወት እንዳለባትም ነው የተናገሩት፡፡

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋርም በካይሮ ውይይት አድርገዋል፡፡

ምንጭ፦ አል አይን ኒውስ